Wednesday, 5 March 2014

አህያ ሸራህያ፤ አግዮስ፤ አካዕ፤ ቤቃ፤ፓንዋማንጦን ወዘተ…የሚሉት አስማተ መለኮት(የመለኮት ስሞች) እውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደሉምን?

+++ ተወዳጆች ሆይ! ሃይማኖተ ክርስቶስ በሆነች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነታችን የሚያምን ሁሉ ትክክለኛውን አስተምሕሮ በጥንቃቄ ቀርቦና ጠልቆ ሊረዳ ይገባዋል:: እስቲ ዛሬ አንዳንድ አብዳን(ሰነፎች) የሚስቱበትን አስማተ መለኮት(የመለኮት ስሞች) እንይ:: ድርሳነ ሚካኤል ላይ ከመጽሐፈ ሄኖክ የተወሰዱ በቅዱስ ሚካኤል ክንፍ ላይ የተጻፉ ኅቡዕ ስሞችን እናገኛለን:: 1ኛ.አህያ ሸራህያ ("ህ" ላልቶ ይነበብ!) በዕብራይስጥ ኤህዬ አሼር ኤህዬ ይባላል:: በግዕዝ ደግሞ እሄሉ ዘእሄሉ ወይም እከውን ዘእከውን ሲባል በአማርኛ "ያለና የሚኖር" ማለት ነው:: ዘፀ.3:14 ላይ እናገኘዋለን:: 2ኛ.አግዮስ የሚለው በጽርዕ(በግሪክ) አጊዎስ ይባላል:: ቅዱስ; ክቡር; ምስጉን ማለት ነው:: 3ኛ.አካዕ በግሪክ አካይዖ ሲባል አምላክ ከሃሊ(አምላክ ሁሉን ቻይ) ማለት ነው:: "ወአንበሮ ለዝ መሐላ አካዕ በእዴሁ ለሚካኤል" እንዲል::ሄኖ.20:1-5:: 4ኛ.ቤቃ ማለት ቀዳሜሁ ቃል(በመጀመሪያ የነበረ ቃል) ማለት ነው:: 5ኛ.አውሎግዮስ ጌርዮስ የሚለው ደግሞ በግሪክ ኤፍሎጊቶስ ኪሪዮስ ይባላል:: ቡሩክ እግዚአብሔር ማለት ነው:: 6ኛ.ጌርዮስ በግሪክ ኪርዮስ ሲባል እግዚእ(ጌታ); እግዚአብሔር ማለት ነው:: 7ኛ.ፓንዋማንጦን በግሪክ(በጽርዕ) ፕኔፍማቶን ይባላል:: መንፈስ(ቅዱስ) ማለት ነው:: ታዲያ በዕብራይስጥ; በግሪክና በግዕዝ ልሳን ስመ አምላክ መጥራቷ; ድርሳናቷ ጥንቆላ አስተምህሮዋ ፀረ-ወንጌል ያስብላል??? ለመሆኑ እነዚህ ስሞች ለእግዚአብሔር ብቻ የሚያገለግሉ አይደሉምን??? ካልተማረ መናፍቅ ይጠብቀን!!!

3 comments:

  1. የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጸሎት የማንኛውም ችግር መፍትሔ እንደሆነ ታስተምራለች። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸልይዋል። ደቀ መዛሙርቱም እንዴት እንደሚጸልዩ ጠይቀውት አቡነ ዘበሰማያትን እዚያው እፊታቸው ደርሶ አስጠንቷቸዋል። ደቀ መዛሙርቱ በጸሎት ኀይል ብዙ ተአምራት ሠርተዋል። እኛንም፥ “ከናንተ ማህል ማንም መከራ ቢደርስበት ይጸልይ፤ ደስተኛም ከሆነ፥ የምስጋና መዝሙር ይዘምር። የታመመም ካለ፥ ካህናትን ይጥራና አከላቱን በዘይት ቀብተው የጌታን ስም ጠርተው ይጸልዩበት። የእምነት ጸሎት በሽተኛን ያድናል” ይሉናል (ያዕ ፭፡፲፫–፲፭)። ይኸ ብቻ አይደለም። ተራ ወይንና ተራ ዳቦ ወደ ቅዱስ የጌታ ደምና ሥጋ የሚለወጠው በጸሎት መሆኑ ከጥንት ጀምሮ የምናምነው ነው።

    የጸሎቱ ዓይነቶች በብዙ ጥንቃቄ እንዳልደረሱን ከአንዳንድ ሁኔታዎች ለመታዘብ ይቻላል። ለምሳሌ፥ ከቅዳሴ በፊት የምትነገር “[በእንተ] ትምህርተ ኅቡኣት” የምትባ አጭር ጸሎት አለችን። የስሟ ትርጓሜ፥ “[ስለ] ድብቅ ነገሮች ትምህርት” ማለት ነው። በዚህ ጸሎት ውስጥ “ተገምረ በማኅፀነ ድንግል ተኀቢኦ ለኵሉ ኀይል እለ በሰማያት ማኅደር ወለእለ ይትቃወማ ኀይል በኢያእምሮ ሰወሮ . . .” (ማደሪያቸው በሰማያት ከሆነው ኀይል ሁሉ ተደብቆ በድንግል ማኅፀን ተቻለ፤ [ታምሩን] የሚቃወማትን ኀይልም በአለማወቅ ደበቀው . . .) የሚል አንድምታ የሚያሻው ንግግር አለበት። ድብቁ ከማን ነው? ከሰይጣን ከሆነ የሰይጣንን ኀይል ማጋነን ነው።

    አንዳንድ ደብተራዎች ከዚህ የሚረዱት ሰይጣን የሚሸነፈው በምስጢር ኀይል ነው የሚል ነው። በዚህ ላይ፥ ቅድስት ማርያም የጸለየቻቸው ጸሎቶች ናቸው የሚባሉ “ባርቶስ” እና “ሰኔ ጎልጎታ” የሚባሉ ንኡሳት መጻሕፍት አሉን። እነዚህና “ነገረ ማርያም”፥ አምላክ የሚሰማው ስውር ስሞቹን (አስማት) እየጠሩ ሲጸልዩለት ነው የሚል ስሕተት አሉባቸው። ድርሳነ ሚካኤልም የሚጸዳ ነገር አለበት።

    “አምላክ የምስጢር ስም የለውም፤ የመጸለያ ምስጢር ስሞች የሚባሉ ቃላት የሉም” ሲሏቸው፥ ክርስቶስ የኢያይሮስን ልጅ ሊያድናት ሲጸልይ፥ “ጣሊታ ኩሚ” (ማር ፭፡ ፵፩)፥ በመስቀል ላይ ሆኖ ሲጸልይ፥ “ኤሎሄ ኤሎሄ ኤልማስ ላማ ሰበክታኒ” (ማቴ ፳፯፡፵፮) ብሎ ስውር ቃላት ተጠቅሟል ይላሉ። ግን እነዚህ ሁሉ ሳይተረጐሙ ተጠቅሰው ነው እንጂ፥ አስማት አይደሉም። ክርስቶስ ይናገርበት በነበረው ቋንቋ የተናገራቸው ናቸው። ተተርጕመው ቢሆን ኖሮ “ጣሊታ ተነሽ ቁሚ”፥ “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ማለቱን እናይ ነበረ።

    በባህል ሲወርድ ሲዋረድ እንደደረሰን፥ አይሁድ ክርስቶስን ሲሰቅሉት በአምስት ምስማሮች (ችንካሮች) ቸንክረውት ነበር። እነዚህ ምስማሮች (ችንካሮች) በግሪክኛ ስም አላቸው፤ (1) ሳዶር፥ (2) አላዶር፣ (3) ዳናት፥ (4) አዴራ፥ (5) ሮዳስ ይባላሉ። እነሱንም የችንካሮቹ ስሞች እንደሆኑ ከማቆየት አልፈው፥ የአምላክ የምስጢር ስሞች ከሚሏቸው አስማት ጋራ ደባልቀው፥ ለመፍትሔ ሥራይ (መርዝና ድግምት ማርከሻ መዳኒት) የጸሎት ክፍል አደረጓቸው።

    ሥራይ የመርዝ ማርከሻ መዳኒት ቢባልም፥ አብዛኛውን ጊዜ በሽታው ርኩስ መንፈስ (ጋኔን) ነው። ጋኔን ሰውን ይይዛል፤ በሽታ ያስለክፋል። በባህላችን እምነት፥ ማናቸውም በሽታ ምንጩ ጋኔን (evil spirit) ነው። ጋኔን የአምላክ ስም ሲጠሩበትና መስቀል ሲያሳዩት ይተናል። ስመ አምላክ ጠርቶ የተጸለየበት ጠበል ጋኔን ካመጣው በሽታ መፈወስ ይቻላል። ጸሎቱን በብራና ላይ ጽፎ በልጅ አንገት ላይ ቢያንጠለጥሉት፥ አጋንንትን ያርቃል። አጋንንት ከሚያመጡት በሽታ ይከላከላል።

    ችግሩ ጸሎቱ ምስጢራዊ ስመ አምላክ መያዙ ነው። አንዳንዶቹ ስሞች ትርጕማቸውና ምንጫቸው አይታወቅም። አንዳንዶቹ ምንጮቻችው ዐረብኛ ነው። ዐረቢኛውን ደኅና አድርገው ካላወቁ፥ እምነትን የሚያናጋ ነገር ሳይቀር ሊቀዱ ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ የአስማት ጸሎር ውስጥ “መሐመድ ስይዱነ” (መሐመድ ጌታችን ነው) የሚል ነገር አገኘሁበት። አንዳንዶቹ ደብተራዎቹ የፈጠሯቸው ይመስላሉ። ለምሳሌ አንድ መጽሐፍ ውስጥ፥ “የመሸን ቀነሸን ያፈዝ ጠርበጡ ራባት ማይ ወልህ ሜድ ርርባል ሚን ካራፉን አሉፍ ፍኑን ሰቂጹን ያህድድ አሴር እምህልና አመጀ በሰልማና አሜን” ይላል። ከዐረብ የጥንቆላ መጽሐፍ ሥርዓት ጠብቆ በጥንቃቄ ያልተቀዳ ሐረግ ሳይሆን አይቀርም።

    ጉዳዩ የጥንትና ሊወገድ የማይቻል የቤተ ክርስቲያናችን ችግር ነው። የተከበሩ መምህራን ሳይቀሩ የዚህ መጥፎ ልምድ ሰለባ ሲሆኑ ይገኛሉ። ባህሉን አጥብቀው ከተቃወሙት ዋናው ከ1426 እስከ 1460 ዓ.ም የነገሠው አፄ ዘርአ ያዕቆብ ነው። ተጋድሎውን (በግዕዝ) እንዲህ ሲል ነግሮናል፤

    “ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ፥ ስሙ፥ እንንገራችሁ፤ በቤተ መንግሥት የነበረውን ዓመፅና ጥንቈላ ከናንተ የደበቅሁት የለም፤ ሁሉንም ነገር ጻፍኩላችሁ እንጂ። ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ፍቅርና ከአምልኮቱ የማበልጠው ነገር የለም። አሁንም በቤተ መንግሥት ስላገኘሁት፥ በወንድሜ በይሥሐቅ ዘመን ስለተጻፈ የአስማት መጽሐፍ እገልጽላችኋለሁ። መጽሐፉ ሁለት ሰዎች ተሸክመውት ሊሄዱ የማይችሉት ትልቅና ከባድ ነው። ተስቦና ማናቸውም ዓይነት በሽታ ሲነሣ፥ የቤተ መንግሥቱ ካህናት ያነቡት ነበረ። ስሞቹ ግን የእግዚአብሔር ሳይሆኑ፥ የሚጠራቸውን እስኪያጠፉት ድረስ የሚረዱ አጋንንት ስሞች ናቸው። እነሆ፥ በእግዚአብሔር ኀይል ደመሰስኩት። ማንኛውንም ሐዋርያት ቈጥረው በሲኖዶሳቸው በሰጡን በሰማኒያ አንድ የሕግ መጻሕፍት ውስጥ የማይገኘውን ስም ከቤተ መንግሥት አጠፋሁ። ወንዶቹንም ሴቶቹንም ልጆቼን እግዚአብሔርን ከማምለክ የሚያስወጡ በሰማኒያ አንዱ የሕግ መጻሕፍት ውስጥ የማይገኙትን ስሞች እንዳይዙም እንዳይደግሙም አስማልኳቸው። ምክንያቱም፥ በጸሎት ጊዜ የጋንንት ስም መጥራት፥ በሌላም ጊዜ ለእርዳታ ማንበብ አጋንንትን ማምለክ ነው። እናንተም የወንጌል ልጆች ሆይ፥ በሰማኒያ አንዱ የሕግ መጻሕፍት ውስጥ የማታገኙትን ስም አትቀበሉ። ሌላ አምላክ በማምለክ እግዚአብሔርን ከማምለክ እንዳይወጡ ኢያሱ የእስራኤልን ልጆች እንዳስማላቸው፥ እኔም የአጋንንትን ስም በመጥራት እግዚአብሔርን ከማምለክ እንዳትወጡ፥በእግዚአብሔር አብ፥ በልጁ በክርስቶስ፥ በሦስተኛው በመንፈስ ቅዱስ አስምላችኋለሁ። ከጦርና ከሌላ አደጋ በአስማት ትድናላችሁ የሚሏችሁን አትስሟቸው። በአስማት ከጦር ይዳን ቢሆን ኖሮ፥ በኮሮጆ በዓሥራ ሁለት ስንዝር፥ በዓሥር ስንዝር በስምንት ስንዝር ክርታስ የተመላ የአጋንንት አስማት ይዞ የመጣው የጥፋት ልጅ በድላይ በዳነ ነበር። በእግዚአብሔር ኀይል በጦር ሜዳ ወደቀ። እኔንም፥ “በጦርነት ጠላትክን የምታሸንፍበትን አስማት እናምጣልህ” ብለውኝ ነበር። እኔ ግን ከእግዚአብሔር ሌላ የሚያድን እንደሌለ ዐውቄ አልተቀበልኳቸውም። እግዚአብሔር በእመቤቴ ማርያም ድንግልና አማላጅነት የጠላቶቼን ድምሳሴ አሳየኝ።”


    ReplyDelete
  2. በእንተ ተዋሕዶ
    በርቱ ተበራቱ አምላከ ቅዱሳን ቅዱስ እግዚአብሔር ይርዳቹ
    ከገፃችሁ ብዙ የሕይወት ስንቅ እያገኘን ነው
    እግዚአብሔር ይስጥልን
    ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡

    ReplyDelete
  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete