Tuesday, 18 March 2014

መጻጉዕ ለምን ትመታኛለህ?

 መጻጉዕ ለምን ትመታኛለህ?

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
          ጌታችንከተጠመቀ በኋላ የአይሁድ ፋሲካ ሦስት ጊዜ ተከብሯል፡፡ የመጀመሪያው ፋሲካ ጌታችን ቤተ መቅደሱን ያጸዳበትና በቤተ መቅደስ ሲሸጡሲለውጡ የነበሩትን ያስወጣበት ሲሆን በመጨረሻው ፋሲካም ሰሞን እንዲሁ ለሁለተኛ ጊዜ ቤተ መቅደሱን አንጽቶ ከፋሲካው ማግስት ተሰቅሏል፡፡በሁለቱ ፋሲካዎች መካከል በነበረው ፋሲካ ደግሞ ጌታችን ወደ ቤተ ሳይዳ መጣ፡፡
            ቤተ ሳይዳየመጠመቂያው ስፍራ ስም ሲሆን ከአጠገቡ ደግሞ በጎች በር ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ዘመነ ኦሪት በግ መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርብበት ነበር፡፡ስለዚህ በዚያ በር መሥዋዕት ሆነው የሚቀርቡ በጎች የሚገቡበት ነበር፡፡ በጎቹ  ነውር እንደሌለባቸው ማለትም ቀንዳቸው እንዳልከረረ ፣ ጥፍራቸው እንዳልዘረዘረ፣ ጠጉራቸው እንዳላረረ እያገላበጡ የሚጠናበት ፣  የአንድ ዓመት ተባዕት/ወንድ/ መሆናቸው የሚታይበት ሥፍራ ነው፡፡ ይህን መስፈርት አሟልተው ያለፉ በጎች ለመሥዋዕትነት  ሲቀርቡ ለዚህ ብቁ ያልሆኑትን ግን ለይተው ፣ በአለንጋ እየገረፉ ያስወጡአቸዋል፡፡
            በቤተ ሳይዳየጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያዪቱ ወርዶ ውኃውን አንዳንድ ጊዜ ያናውጥ ነበር፡፡ ይህ መልአክ ‹በሰው ቁስል ላይ የተሾመ ፣ በበሽታምላይ ሁሉ የተሾመ› የስሙም ትርጓሜ ‹እግዚአብሔር ፈዋሽ ነው› ማለት የሆነ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነበር፡፡መልአኩ ውኆችን ለመቀደስ ፣ ጸሎትን ከሰው ወደ ፈጣሪ ለማድረስ ወደ ውኃው ይወርድ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ውኃ በራሱ ማዳን ባይቻለውምቅዱሳን መላእክት የነኩት እንደሆነ በረከትና ፈውስ እንደሚሠጥ የሚያስረዳን ነው፡፡ ውኃው ከተነዋወጠ በኋላ ግን መዳን የሚቻለውመጀመሪያ መግባት ሲቻል ነበር፡፡ በዚህ የጠበል ሥፍራ በነበሩ አምስት መመላለሻዎች  ‹በሽተኞች ፣ አንካሶች ፣ ዕውሮችና እግራቸው የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር፡፡በተለይ ደግሞ አንካሶች ፣ ዕውሮችና እግራቸው የሰለለ ሰዎች በቁጥር የሚበዙት ከሌላው በሽተኛ በተለየ እነሱ የውኃውን መንቀሳቀስአይተው ለመግባት እንዳይችሉ ወይ ዓይናቸው ማየት አይችልም ፤ ያም ባይሆን መንቀሳቀስ ያቅታቸዋል፡፡ ገብተውም እንኳን ቢሆን ድንገትከእነሱ ቀድሞ የገባ ሰው ካለ እነሱ ስለማይፈወሱ ከውኃው መልሶ የሚያወጣቸውም ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡ አለዚያ ገብተውም አውጪ አጥተውሊቸገሩ ይችላሉ፡፡ ምናልባትም በእንዲህ ዓይነት ችግር ለባሰ ነገር የተዳረገም ሊኖር ይችላል፡፡
            ከእነሱቀድሞ የሚድነው እንግዲህ ሁለት ዓይነት ሰው ነው፡፡ አንደኛው በሽታው ለመንቀሳቀስ የማያግደው ሆኖ እያለ የእነሱ ይብሳል ብሎ ሳያዝንየሚገባ ነው፡፡ መቼም ሰው እንኳን ቀድሞ የገባ ሰው ብቻ በሚድንበት ሥፍራ ቀርቶ ፤ በማንኛውም ሰዓት ቢገባ በሚዳንበት የጠበልሥፍራ ‹ከእኔ በሽታ የእገሌ ይብሳል ፤ እስቲ ቅድሚያ ልስጠው› ሲል ብዙ ጊዜ አይታይም፡፡ ስለዚህ እነዚህን ደካሞች ቀድሞ የሚገባበሽተኛ ብዙ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ወደ መጠመቂያው ሊወረውሩት የሚጠባበቁ ዘመዶች ያሉት ፣ አለዚያም ዘመድ የሚያፈራበት ገንዘብያለው በሽተኛ ደግሞ ሌላው ቀድሞ ወደ መጠመቂያው የሚገባ ነው፡፡
            በዚህ ሥፍራለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል የተኛ በሽተኛ (መጻጉዕ) ነበር፡፡ እንግዲህ ሠላሳ ስምንት ዓመት ማለት የጉልምስና ዕድሜ ነው፡፡መጻጉዕ የመጣው በዐሥር ዓመቱ ነው እንኳን ብንል አሁን አርባ ስምንት ዓመቱ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጌታችን በኋላ ‹የሚብስ እንዳይደርስብህደግመህ ኃጢአትን አትሥራ › ብሎ ስለተናገረ ከመታመሙ በፊት ለዚህ ጽኑ ደዌ የሚዳርግ ኃጢአት ለመሥራት የሚችልበት ዕድሜ ላይ ደርሶአልማለት ነው፡፡ መቼም ክፉ ደግ በማያውቅበት ሕጻንነቱ በድሎ ‹‹የልጅነቱ መተላለፍ ታስቦበት›› ታመመ ብሎ መናገር ይከብዳል፡፡ ብቻይህ ሰው የአንድ ጎልማሳ ዕድሜ ያህል በአልጋ ላይ ሆኖ በቤተ ሳይዳ ተኝቶአል፡፡ ጠበል ሊጠመቅ ሲጠባበቅ በጸጉሩ ሽበት ፣ በግንባሩምልክት አውጥቶአል፡፡
            ከሁሉ የሚያሳዝነውደግሞ ይህ ሰው አልጋው ላይ ሆኖ እጅግ ብዙ ሰዎች ሲፈወሱ መመልከቱ ነው፡፡ ከእሱ በኋላ መጥተው ከእሱ በፊት ድነው የሚሔዱ ሰዎችንማየት እንዴት ይከብደው ይሆን?  እንደሱ ብዙ ዘመን የቆዩት ሲድኑሲያይ ተስፋው ሊለመልም ይችላል፡፡  በመጡ በአጭር ጊዜ ዘመደ ብዙበመሆናቸው ብቻ የሚድኑ ሰዎችን ሲያይ ግን ልቡ በኀዘን ይሰበራል፡፡ ዓመቱ በረዘመ ቁጥር ተስፋ ቆርጦ ቤተ ሳይዳን ቤቴ ብሎ ከመኖርበስተቀር ምንም የሚታየው ነገር አይኖርም፡፡ እግዚአብሔርን በመከራው ውስጥ ተስፋ እያደረገ ይጽናናል አንዳንል ደግሞ እንደ ጻድቁኢዮብ ወይም እንደ በሽተኛው አልዓዛር ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበረው ቢሆን ኖሮ መቼ ለዚህ በሽታ የሚዳርገው ኃጢአትይሠራ ነበር?  ስለዚህ በቃለ እግዚአብሔር ይጽናናል ማለትም ያስቸግራል፡፡ያም ሆነ ይህ ይህ ሰው እጅግ ተሰቃይቶ ነበር፡፡
            ጌታችንየዚህን ሰው ችግር ብቻ ሳይሆን ብዙ ዘመን እንደዚህ እንደነበረ ያወቀው ማንም ሳነግረው ነበር፡፡ በሽታውን ከነመንሥኤው አስቀድሞያውቃልና ወደዚህ የብዙ ዓመታት በሽተኛ መጣና ‹ልትድን ትወዳለህን?› አለው፡፡  ጌታችን የሚፈልገው ይህንን ሰው መፈወስ እንጂ የራሱን ማንነት ማሳየት ስላልነበረ‹ላድንህ ትወዳለህን?› አላለውም፡፡ በዚያ ላይ ይህ ሰው የጌታን ማንነት አያውቅም፡፡ ጌታችን ‹ስታምኑብኝ ብቻ ነው የምፈውሳችሁ›የሚል አምላክ አይደለም ፣ ለሁሉ ፀሐይን የሚያወጣ ፣ ለሁሉ ዝናምን የሚያዘንም አምላክ ይህንን ሰውም ለመፈወስ እስኪያምነውም አልጠበቀም፡፡
            ይህ በሽተኛ‹ልትድን ትወዳለህን?› ሲባል የሠጠው መልስ እጅግ የሚያስገርም ነው፡፡ እንደሚታወቀው በሽታ አመል ያጠፋል፡፡ በሽታው በቆየ ቁጥርደግሞ መራር ያደርጋል፡፡ ሰዎች በበሽታ ሲፈተኑ በሰው በፈጣሪም ላይ ብዙ የምሬት ንግግር ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ ጌታችን ‹ልትድን ትወዳለህን?›ብሎ ሲጠይቀው ‹ታዲያ መዳን ባልፈልግ ጠበል ቦታ ምን አስቀመጠኝ? እያየኸኝ አይደል... › ወዘተ ብሎ ብዙ ያለፈ ንግግር ሊናገርይችል ነበር፡፡ ይህ ሰው ግን ምንም የምሬት እና የቁጣ ቃል አልተናገረም፡፡ ጌታችንም ሲያናግረው በጨዋ ሰው ደንብ ‹ጌታ ሆይ..›ብሎ ነው የመለሰለት፡፡  በዚህ ሁኔታው ትሑት ሊባል ይችላል፡፡
            ነገር ግንየመለሰው የተጠየቀውን አይደለም፡፡ ጥያቄው ‹ልትድን ትወዳለህን?› የሚል ከሆነ መልሱ ‹አዎ መዳን እወዳለሁ› አለዚያም ‹አይ አልፈልግም›መሆን ነበረበት፡፡ እሱ ግን ‹ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት።› እንግዲህ የጌታችንን ማንነት ባይረዳውም ጌታችን በወቅቱ የሠላሳ ሁለት ዓመቱነበርና ‹ምናልባት ወደ መጠመቂያው ሊጨምረኝ አስቦ ይሆናል ያም ባይሆን ግን ከተከተሉት ሰዎች አንዱን አደራ ሊልልኝ ይሆናል› ብሎአስቦ ነበር፡፡ ‹ሰው የለኝም› ብሎ የሠላሳ ስምንት ዓመታት ብሶቱን ተናገረ፡፡ ‹ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል› ብሎ እያየ የቀደሙትንሰዎች አስታወሰ፡፡
            ጌታችን ‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ› አለው፡፡ ባላሰበውባልጠበቀው መንገድ ፈወሰው፡፡ ይህ ሰው ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ ሲጠባበቃት የነበረችውን የቤተ ሳይዳ ጠበል ሳያገኝ ፣ በመልአኩመውረድ ሳይሆን በመላእክት ፈጣሪ ቃል ተፈወሰ፡፡ ገባሬ መላእክት ክርስቶስ ራሱ መጥቶ አዳነው፡፡ ይህ ሰው እግዚአብሔር በዚህችጠበል ካልሆነ በቀር በሌላ በምንም መንገድ ያድናል ብሎ አስቦም አልሞም አያውቅም ነበር፡፡ ለመዳን የሚያስፈልገው ምንድን ነው ተብሎቢጠየቅ የሚመልሰው ‹ወደ ውኃው የሚጨምር ሰው እና የቤተ ሳይዳ ውኃ› ብሎ ነበር፡፡ ጌታችን መጻጉዕ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ተስፋያደረጋትን ጠበል ወይም ደግሞ ወደ ጠበሉ የሚጨምሩትን ሰዎች ሳይጠቀም ፈወሰው፡፡ እግዚአብሔር ያለ ጠበልም እንደሚያድን ማመን ካልቻልንእምነታችን ሙሉ አይደለም፡፡  ይህ ሰው ወደ ውኃው ገብቶ ቢድን ኖሮ‹ጌታዬ አዳነኝ› ከማለት ይልቅ ‹‹መዳን ይነሰኝ? ሠላሳ ስምንት ዓመት እኮ ነው የጠበቅኩት...›› እያለ ልፋቱን ያወራርድ ነበርእንጂ ፈጣሪውን አያመሰግንም ነበር፡፡
            ጌታችንጠበል ቦታ ያገኘውን ያለ ጠበል ፈወሰው ሲባል መቼም ጠበል መጠመቅ የማይወዱ ወይም በጠበል የማያምኑ ሰዎች ደስ ሊላቸው ይችላል፡፡‹‹እኛስ ምን አልን ጌታ እኮ ይህን በሽተኛ ጠበል ቦታ አግኝቶ እንኳን የፈወሰው ያለ ጠበል ነው›› ብለው ባቀበልናቸው በትር ሊመቱንይፈልጉ ይሆናል፡፡ ሆኖም እዚሁ ዮሐንስ ወንጌል በዘጠነኛው ምዕራፍ ላይ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ጠበል በሌለበት ሥፍራ አግኝቶትእኛ እመት (እምነት) የምንለውን አፈር በምራቁ ለውሶ ከቀባው በኋላ ‹ሒድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ› ብሎ ልኮታል፡፡ ጠበል ምንምየማያስፈልግ ቢሆን ኖሮ ዓይነ ስውሩን ሰው ወደ ወንዝ ወርደህ ተጠመቅ ብሎ አይልከውም ነበር፡፡ ዛሬ ለታመሙ ሰዎች ጠበል ሒዱ ብለንስንመክር ክርስትና ያልገባን ፣ ክርስቶስን የማናውቅ የሚመስለው ይኖራል፡፡ አሁን ባየነው ታሪክ ውስጥ ግን ለበሽተኛው ‹ጠበል ሔደህተጠመቅ› ብሎ የመከረው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ መፈወስ የሚቻለው ክርስቶስ ጠበል ተጠመቅ ብሎ ከተናገረ ፤ የታመመንመፈወስ የማንችለው እኛ ኃጢአተኞቹ ከንፈር ከመምጠጥ ይልቅ ሔደህ ተጠመቅ ብንል ምን አጥፍተናል? ጌታችን ሲያደርግ ያየነውን ነው፡፡እኔን ምሰሉ ብሎ የለ እንዴ? (ዮሐ. 9፡7)
            በእነዚህሁለት ታሪኮች ግን ጌታችን ሲፈልግ በጠበል ሲፈልግ ያለ ጠበል ፤ ሲሻው በምክንያት ሲሻው ያለ ምክንያት፡፡ ሲፈልግ በጠበል ሲፈልግበህክምና ፤ ሲፈልግ በቃሉ ሲፈልግ በዝምታ ፣ ሲፈልግ በቅዱሳን መላእክቱ ሲፈልግ ያለ ቅዱሳን መላእክቱ ማዳን እንደሚቻለው እንረዳለን፡፡
            ጌታችንለመጻጉዕ ‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ› ብሎ ሲነግረው ወዲውኑ ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሔደ፡፡ እዚህ ላይ አባታችን ቅዱስ ዮሐንስአፈወርቅ እንዳደረገው የበሽተኛውን እምነት እናደንቃለን፡፡ ራሱን መሸከም የማይችለው ይህ በሽተኛ ተነሣና አልጋህን ተሸከም ሲባልአልሳቀም፡፡ ‹እንዴት አድርጌ ነው ደግሞ አልጋ የምሸከመው› ብሎ አልጠየቀም፡፡ በፍጹም እምነት ተነሣና ተሸክሞ ሔደ፡፡ የሠላሳስምንት ዓመት ጓደኛውን ፣ ሰው ሳይኖረው አብራው ኖረችውን ፣ የተሸከመችውን ባለ ውለታው የሆነችዋንአልጋ ተሸክማት አለው - ተሸክሞ ሔደ፡፡
            አንድ ሰው እንኳን ለሠላሳ ስምንትዓመታት ይቅርና ለሠላሳ ስምንት ቀናት እንኳን ቢታመም እንደተሻለው ተነሥቶ አልጋ አይሸከመምም፡፡ እስከሚያገግም ድረስ በደንብ መንቀሳቀስአይችልም፡፡ ራሱን ያዞረዋል ፣ ደክመዋል፡፡ የቀረ ሕመም አያጣውም፡፡ መጻጉዕ ግን የተፈወሰው ያለ ቀሪ በሽታ (ያለ ተረፈ ደዌ)ነበር፡፡ ስለዚህ ወዲያው ተነሥቶ አልጋውን እንዲሸከም ነገረው፡፡ መምህር ኤስድሮስ እንዳሉት ያንን የብረት አልጋ ተሸክሞ እየሔደየጌታን ጽንዐ ተአምራት አሳየ፡፡ ጌታችንም ከዛ በሽታ ያዳነው በነጻ መሆኑን በሚያሳይ ሁኔታ ያችን አንዲት ንብረቱንም ተሸክመህሒድ አለው፡፡
            መጻጉዕ የተሸከመችህን አልጋ ተሸከምተባለ፡፡ አግዚአብሔር የተሸከሙንን እንድንሸከም የሚፈልግ አምላክ ነው፡፡ ውለታ ሳንረሳ የተሸከሙንን ወላጆቻችንን የተሸከመችንንቤተ ክርስቲያንን ፣ የተሸከመችንን ሀገራችንን እንድንሸከም ይፈልጋል፡፡ በአንዱ ሊቅ ደግሞ ‹ዓለም እንደዚህ ናት ፤ እናት ዓለምአልጋ መጻጉዕን እንደተሸከምኩህ ተሸከመኝ አለችው› ብለው ተቀኝተዋል፡፡ (ይህችን ጽሑፍ በምጽፍበት ወቅት ያለሁት በቅርብ መጽሐፉንማግኘት በማልችልበት ሥፍራ ስለሆነ ቅኔውን ማካተት አልቻልኩም ፤ ዝክረ ሊቃውንት 2 ላይ ነው ያለው) 
            እዚህ ላይ ጌታችን ቤተ ሳይዳ ከመጣአይቀር ሁሉንም በሽተኛ መፈወስ ሲችል ለምን አንዱን ብቻ ፈውሶ ሔደ? ብለን ማሰባችን አይቀርም፡፡ የበለጠ የሚያሳዝነው ደግሞ ሊቃውንቱእንደጻፉት የቤተ ሳይዳው መጠመቂያ ፈውስ ከዚያ በኋላ ብዙም አልቆየም፡፡ የመልአኩም መውረድ ቆሞአል፡፡ ከዚያ በኋላ በሰባ ዓመተምሕረትም ኢየሩሳሌም መቅደስዋ ፈርሶአል ተመሰቃቅላለች፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስም የዮሐንስ ወንጌልን ሲጽፍ ‹‹ቤተ ሳይዳ የምትባልአንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት።... ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር።... ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆንነበር።›› ብሎ በኃላፊ ኃላፊ ግሥ  /past perfect tense/ ነበር፡፡ ታዲያ ምነው ጌታችን እንዲህ መሆኑን እያወቀ መጻጉዕን ብቻ ፈውሶት ሔደ? ቢባል የፈወሰው እሱን ብቻ አይደለም፡፡እሱን በሥጋ ቢፈውሰውም ተአምራቱን አይተው በማመናቸው በነፍሳቸው የተፈወሱ ይበዛሉ፡፡ ‹ሕሙማነ ሥጋን በተአምራት ሕሙማነ ነፍስንበትምህርት እየፈወሰ› እንዲሉ አበው በዚያ ሥፍራ በሥጋ ታመው በነፍሳቸው አምነው የዳኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ የጌታችንና የእርሱ አካልየሆነች የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ሥራ ነፍስን መፈወስ እንጂ ሥጋዊ በሽታን መፈወስ ብቻ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው እንጂ ጌታችንሰው ሆኖ ይህችን ምድር በእግሩ ሲረግጥ በሽታ እንዳይኖር ያደርግ ነበር፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ ‹በመስቀል ላይ በቆሰልኸው ቁስል ከኃጢአቴቁስል አድነኝ› ብሎ እንደጸለየ እኛም የዘወትር ልመናችን ለሚከፋው ለነፍሳችን በሽታ ነው፡፡
            በመጻጉዕ ታሪክ ውስጥ ብዙ ቀሪ ነጥቦችቢኖሩም ሁለት ነገሮችን ብቻ እናንሣና ይህችን አጭር ጽሑፍ እንግታ፡፡ ይህ ሰው ተፈውሶ አልጋውን ተሸክሞ ሲሔድ ሰንበት ለሰው ድኅነትእንደተፈጠረች ያልተረዱ አይሁድ በቁጣ ነደዱ፡፡ ‹‹ሰንበት ነው አልጋህን ልትሸከም አልተፈቀደልህም›› አሉት፡፡ ልብ አድርጉ ይህሰው በቤተ ሳይዳ ሠላሳ ስምንት ዓመታት ሙሉ ሲማቅቅ እንደኖረ የሰውን ገመና አዋቂ ነን ባዮቹ አይሁድ ይቅሩና ቤተ ሳይዳን የረገጠሰው ሁሉ ያውቃል፡፡ ላለፉት ሠላሳ ስምንት ዓመታት ወደዚያች የመጠመቂያ ስፍራ ሲሔዱ ያም ባይሆን በጎች ታጥበው ተመርጠው ወደሚገቡበትወደ በጎች በር ሲያልፉ ይህን በሽተኛ በአልጋው ተጣብቆ ሳዩት አይቀሩም፡፡ አሁን ግን ከአልጋው ተነሥቶ የተሸከመችውን አልጋ ተሸክሞበአደባባይ ሲያዩት የጠየቁትን ጥያቄ ተመልከቱ፡፡ ‹‹እንኳን ለዚህ አበቃህ ፤ ዛሬ መልአክ ወረደ ማለት ነው?›› ‹‹እሰይ ልፋትህንቆጠረልህ!›› ያለው የለም፡፡ የተናገሩት አንድ ዐረፍተ ነገር ነው፡፡ ‹‹ሰንበት ነው አልጋህን ልትሸከም አልተፈቀደልህም›› የሚልብቻ!!! ለእነሱ ድኖ ሠላሳ ስምንት ዓመት የተኛበትን አልጋ  ከመሸከሙይልቅ ሰንበት ማፍረሱ ትልቅ ዜና ነው፡፡
            መጻጉዕ ‹ያዳነኝ ያ ሰው አልጋህንተሸከም አለኝ› አላቸው፡፡  እስቲ በደንብ አስተውሉ፡፡ እነዚህ ሰዎችይህን በሽተኛ ፈጽሞ አያውቁትም ነበር እንበል፡፡ እንደዛ ከሆነ ‹ያዳነኝ ሰው› ሲላቸው ‹ከምንድን ነው የምትድነው? ምን ሆነህነበር? ከየት ነው የመጣኸው?› ይሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ መዳኑን ማየት አልፈለጉም እንጂ ማን እንደሆነ ጠንቅቀውያውቁታል፡፡ ከዚያም ‹‹ያዳነኝ ያ ሰው አልጋህን ተሸከም አለኝ›› ሲላቸው ‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሒድ ያለህ ሰው ማን ነው?››ብለው ጠየቁት፡፡ እስቲ ጥያቄና መልሱ ውስጥ ያለውን ሽሽት እንመልከት፡፡ ‹‹ያዳነኝ ሰው አልጋህን ተሸከም አለኝ›› ለሚለው መልስተከታዩ ጥያቄ  ‹ማን ነው ያዳነህ?› የሚል ነበር፡፡ እነሱ ግን የጌታንየማዳን ሥራ ላለመስማት ጆሮአቸውን ደፍነው ስለነበር ‹አልጋህን ተሸከም ያለህ ማን ነው?› አሉ፡፡ የማዳኑን ሥራ እያዩ ከማመንይልቅ መከራከር ፣  ከማድነቅ ይልቅ የትችት ሰበብ መፈለግ እንግዲህጌታን የሰቀሉ የአይሁድ ጠባይ ነው፡፡
            የመጨረሻው ነገር መጻጉዕ ከዚህ በኋላወደ አይሁድ ሄዶ ጌታን መክሰሱና ለጌታ ሞት የመማከራቸው ምክንያት መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሰው ‹የሚብስ እንዳይገጥምህ ደግመህ ኃጢአትንአትሥራ› ብሎ ጌታ ቢያሳስበውም አልሰማም፡፡ ጌታ በተያዘበት በምሴተ ሐሙስ ለሊቀ ካህናቱ አግዞ ጌታችንን በጥፊ መታው፡፡ ጌታችንም‹‹ክፉ ተናግሬ እንደሆነ ስለ ክፉ መስክር መልካም ተናግሬ ከሆነ ግን ስለምን ትመታኛለህ?››  አለው፡፡ (ዮሐ.18፡23) ‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሒድ ከማለት በቀር ክፉቃል ተናግሬህ ከሆነ መስክርብኝ ፤ የተናገርኩህ መልካም ሆኖ ሳለ ስለምን ትመታኛለህ›› ማለቱ ነበር፡፡ ጌታችን በማግሥቱ ያ ሁሉጅራፍና ግርፋት ሲደርስበት አንድም ጊዜ ‹‹ለምን ትመታኛለህ›› ብሎ አልተናገረም፡፡ የመጻጉዕ ጥፊ ይህን ያህል ዘልቆ የተሰማውለምንድር ነው?
            የመጀመሪያው ምክንያት ከቤተ ሳይዳከበጎች በር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ጌታችን የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ነው፡፡ በበጎች በር አልፎ የመጣውንጹሐ ባሕርይ እንደሆነ ለማስረዳት ነበር፡፡ ለዚህም ንጽሕናው ዋነኛው ምስክር ፈውስን የሠጠው ይህ በሽተኛ ነበር፡፡ እሱ ግን መታው፡፡‹‹በቤተ ሳይዳ ክፉ ቃል ተናግሬህ ከነበር መስክርብኝ› ማለቱ  ‹ነውርየሌለብኝ ፣ ለመሥዋዕት የተዘጋጀሁ በግ ነኝ ለምን ትመታኛለህ?› ማለቱ ነበር፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከሮማውያን ግርፋት በላይለጌታ ዘልቆ የሚሰማው ባዳነው ሰው መመታቱ ስለሆነ ነው፡፡ ውድ አንባቢያን መጻጉዕ ከሠላሳ ስምንት ዓመት በሽታ ብቻ ዳነ ፣ እኛግን የዳንነው ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በሽታ ነበር፡፡ ጌታችን እኛን ያስነሣን ከሲኦል አልጋ ነው፡፡ ከሌላው ሰው ይልቅእግዚአብሔር የእኛ ዱላ ይሰማዋል፡፡ ይህም ዱላ ኃጢአታችን ነው፡፡ እግዚአብሔር ዛሬም ድረስ ለእያንዳንዳችን ይጠይቃል፡፡ ‹‹ለምንትመታኛለህ?››
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ


No comments:

Post a Comment