ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
አንድደብዳቤ ከሌላ ሀገር ቤታችን ድረስ በመልእክተኛ እጅ መጣ እንበል፡፡ ደብዳቤው አራት ገጽ ነው፡፡ በዚህ ደብዳቤ ውስጥ ‹በደስታእጸልያለሁ!› ‹ደስ ብሎኛል› ‹ደስታዬን ፈጽሙልኝ› ‹ደስታዬና አክሊሌ› ‹ደስ ይበላችሁ እደግመዋለሁ ደስ ይበላችሁ!› የሚሉ በርካታየደስታ መልእክቶች ተሞልተው ብናይ ‹ይህን ደብዳቤ የጻፈው ሰው እንዴት ቢመቸው ነው?› ብለን መደነቃችን ፣ በደስታውም መደሰታችንአይቀርም፡፡ የፊልጵስዩስ ምእመናን የገጠማቸው ይኼ ነው፡፡ መምህራቸው ቅዱስ ጳውሎስ የላከላቸው ባለ አራት ምዕራፍ መልእክት ደስታየሚለው ቃል ዐሥራ አምስት ጊዜ የተጻፈበት ነበር፡፡ መልእክቱን በደስታ ጀምሮ በደስታ ነበር የጨረሰው፡፡ ከሁሉ የሚያስደንቀው ነገርግን ቅዱስ ጳውሎስ ይህን በደስታ የተሞላ ደብዳቤ የጻፈው እስር ቤት ውስጥ ሆኖ ነበር፡፡
አንድሰው ከእስር ቤት ውስጥ ሆኖ ደብዳቤ የመጻፍ እድል ቢሠጠው ምን ብሎ ይጽፍ ይሆን? ‹‹ምግብ አልተስማማኝም ፣ ተባዩን አልቻልሁትም፣ መኝታው አልተመቸኝም ፣ ፈጣሪዬ ቢገድለኝ ይሻል ነበር›› ይል ይሆን? ለነገሩ ላይልም ይችላል፡፡ የሆዱን በሆዱ ይዞ ‹‹አይዞአችሁአታስቡ ፣ ሁሉም ያልፋል ፣ እኔ ደህና ነኝ›› ይልም ይሆናል፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ግን በአንድ ደብዳቤ ዐሥራ አምስት ጊዜ ደስይበላችሁ ብሎ ደብዳቤ የሚልክ ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ አንድ እስረኛ እንዲህ ብሎ ቢጽፍ እንኳን ቤተሰቦቹ ጤንነቱን መጠራጠርይጀምራሉ፡፡ ‹ተስፋ ቆርጦ ይሆን? በራሱ ምን ክፉ ነገር ሊያደርግ አሰበ? ሊሰናበተን ይሆን› ብለው ሊጨነቁም ይችላሉ፡፡ ሐዋርያውይህን ደብዳቤ የጻፈው ከታሠረ ሦስተኛ ዓመቱ ላይ ነበር፡፡ ስለዚህ ገና የእስር ቤትን ችግር ስላላየ ነው ሊባል አይችልም፡፡ አንዳንዱእስረኛ ደብዳቤ ቢጽፍ ‹ምነው እነ እገሌ መጥተው አልጠየቁኝም ፣ እነ እገሊትስ አብረን በልተን ጠጥተን እንዴት ይረሱኛል?ልውጣ ብቻ› ብሎ ሊያማርር ይችላል፡፡ ደስተኛው ቅዱስ ጳውሎስ ግን ባልጠየቁት ሰዎች አላማረረም፡፡ እንዲያውም በሦስተኛ ዓመት ላይያስታወሱት በመሆኑ ሳይበሳጭ ‹‹ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁእንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር።›› ብሏል፡፡ (ፊል. 4፡10) የዚህ ሁሉ ደስታው ምክንያት ምን ነበር?
መታሰርለሐዋርያት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ሁሉም ስለ ወንጌል ታስረዋል ፣ ተግዘዋል ፣ ተገርፈዋል ፣ ሞተዋል፡፡ በሚያስተምሩበት መድረክቃለ ሕይወት ያሰማልን ከመባል ይልቅ የሚጠብቃቸው ዱላና ጅራፍ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሲደርስባቸው ግን ጠጅ እንደጠጣ ጮማ እንደቆረጠሰው ፊታቸው በርቶ ፣ ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ ስለተገባቸው ደስ ይላቸው ነበር፡፡ የደስታቸውም ምክንያት በሚደርስባቸው መከራ ሳይሆንበሚያገኙት ዋጋ ፣ በሚጠብቃቸው ጸጋ ‹በጌታ› ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በሮም ታስሮ እስር ቤት በየስድስት ሰዓቱ እየተቀያየሩ በፈረቃየሚጠብቁት የንጉሥ ዘበኞች ነበሩ፡፡ ‹‹እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም›› ያለው ይህሐዋርያ በፈረቃ የሚጠብቁትን ዘበኞች በፈረቃ ያስተምራቸው ነበር፡፡/2ጢሞ.2፡9/ እስር ቤትን ጉባኤ ቤት ፣ ወህኒውን ቅኔ ማኅሌት ማድረግ የነጳውሎስ የእነሲላስ ዋነኛ ሥራ ነውና ቢታሰርም አልከፋውም፡፡ይልቁንም ከራሱ አልፎ እኛንም ደስ ይበላችሁ አለን፡፡
ቅዱስጳውሎስን ሌላ ያስደሰተው ነገር ቢኖር በውጪ ያለው አገልግሎት አለመታጎሉ ነው፡፡ እውነተኛ መምህር ነውና ከእርሱ መታሰር ይልቅየሚያስከፋው የጉባኤው መፈታት ነው፡፡ ስለዚህ እኔ ከሌለሁ ጥቅሜን ይረዱታል የሚል ምቀኝነት በእርሱ ዘንድ ስለሌለ የትምህርቱ አለመቋረጥደስ አለው፡፡ የሰባኪዎቹ ማንነትና ዓላማ የተለያየ ቢሆንም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ክርስቶስ ይሰበካል ፤ ስለዚህ ደስ ብሎኛል›› አለ፡፡የቅዱስ ጳውሎስ የደስታ ምክንያቶች ብዙ ናቸውና መጽሐፉን ለአንባቢ በመተው በእርሱ የእስር ቤት ቆይታ ወቅት የነበረውን የሰባኪዎችሁኔታና ዓላማ እንመልከት፡፡
ቅዱስጳውሎስ በመልእክቱ ስላሰሩት ሮማውያን ሳይሆን ‹በጌታ ስላሉቱ ወንድሞች› ወይም ከክርስቲያኖች ወገን ስለሆኑት ክርስቶስን ስለሚሰብኩትአገልጋዮች በሁለት ወገን አድርጎ ተናገረ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ወገኖችበቁጥር የሚበዙት ሲሆኑ ‹ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ› ‹ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስንይሰብኩታል› ‹ስለ ወንጌል መመከቻ ለማድረግ እንደተሾምኩ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ› በማለት የገለጻቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖችጳውሎስ የታሰረው ለሹመት ለሽልማት ሳይሆን ለአምላኩ ብሎ እንደሆነ አስበው ‹በሱ ላይ የደረሰ ከደረሰብንም ይድረስብን› ብለው ወስነውእንደ አንበሳ ሳይፈሩ የሚሰብኩ ናቸው፡፡ ስብከታቸውም በበጎ ፈቃደኝነት ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ወንጌል የቆመ ሐዋርያ መሆኑንበማሰብ የእሱን መከራ እያሰቡ በመጽናናት የሚያገለግሉ ቅን አገልጋዮች ናቸው፡፡
ሁለተኛዎቹደግሞ ‹ከቅንአትናከክርክር ፣ በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸውየሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ።›ብሎ የገለጻቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ስለ ክርስቶስ የሚሰብኩት ለክርስቶስ ካላቸው ፍቅር ሳይሆን ለጳውሎስ ካላቸው ጥላቻ የተነሣነበር፡፡ ‹እሱ ኖረ አልኖረ ወንጌል መቼ ቀረ› እያሉ ለማሳጣት ፣ ወንጌል ያለ ኦሪት ጥምቀት ያለ ግዝረት አትጠቅምም እያሉ ለማሳሳት፣ ሐዋርያውም ‹በእስራቱ ላይ ኀዘን ይጨመርበት ይበሳጭ ፣ ይቃጠል› ብለው ስለ ክርስቶስ ይሰብኩ ነበር፡፡ ክርስቶስን ቢወዱ ኖሮ ስለ ክርስቶስ ታስሮ እየተሰቃየ ያለውን ጳውሎስንም ይወዱነበር፡፡ ለክርስቶስ ያላቸው ፍቅር ልባዊ ስላልሆነና ዓላማቸው ስለ ክርስቶስ መስበክ ስላልነበር ክርስቶስን መስበክን ‹ለቅንዓት፣ ለክርክር ፣ ለጥላቻ› ተጠቀሙበት፡፡
ተመልከቱጳውሎስ ጫማው እንደ ሽንኩርት እስከሚላጥ ዞሮ ያስተማረ ፣ በአይሁድ ዘንድ የነበረውን ዝናና ክብር ፣ እንደሮማዊነቱ የነበረውንስፍራ ስለጌታው ትቶ በፍጹምነት ያገለገለ አባት ነው፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲገደል ቁጭ ብሎ ልብስ ሲጠብቅ የነበረው ይህ ሰው ‹የሚያደርጉትንአያውቁምና ይቅር በላቸው› በሚለው የእስጢፋኖስ ምልጃ ይቅርታ አግኝቶ የአይሁድን ልብስ ከመጠበቅ የክርስቶስ ልብስ የተባሉ ምእመናንንወደመጠበቅ የተሻገረ እረኛ ነው፡፡ (‹አልባሲሁሰ ለክርስቶስ መሃይምናን እሙንቱ› ይላል ብዬ ነው፡፡) ጌታ ‹ምርጥ ዕቃ› ብሎ የጠራውን ቅዱስ ጳውሎስን ጠልቶ ክርስቶስን መስበክእንዴት ይቻላል? ጌታስ ምርጥ ዕቃውን እየወረወሩ እናከብርሃለን ቢሉት እንዴት ይቀበለዋል?እንኳን ምርጥ ዕቃውን አጥሩን እንኳን መነቅነቅ ባለቤቱን መናቅ ነው እንላለን አይደል?እነሱ ግን ይህን አደረጉ፡፡ አጥሩን ነቀነቁ ፤ ባለቤቱንም ናቁ!
የዘመናችንምየስብከት ሁኔታ ይህ ዓይነት ችግር እየከበበው ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው ዛሬ ቅዱስ ጳውሎስ ያለው እስር ቤት ውስጥ አይደለም፡፡ከወህኒ ብቻ ሳይሆን ከዚህች ዓለም እስር ተፈትቶ ፣ የዓለምን ማሰሪያ ሐምሌ አምስት ቀን በሰይፍ በጣጥሶ ‹ልሔድ ከእርሱ ጋር ልኖርእናፍቃለሁ› ወዳለው ክርስቶስ ሔዷል፡፡ እሱ አይኑር እንጂ በሱ ዘመን የነበረው የሰባኪዎች ዝንባሌ በእኛም ዘመን እየታየ ነው፡፡በዚያ ዘመንየነበሩት ጳውሎስን የሚወዱና ጳውሎስን የማይወዱ ሰባኪዎች ነበሩ፡፡ በእኛ ዘመን ደግሞ ቅዱሳንን የሚወዱና ቅዱሳንን የማይወዱ ሰባኪያንሆኖ ሰፍቶአል፡፡
እናም ስለ ክርስቶስ መናገር ማለት ስለ ቅዱሳን አለመናገር የሚመስላቸው ፣ ከፍ ሲልም የቅዱሳንንስም ማንሳት የሚጠየፉ ‹በፍቅር የማይሰብኩ› ወገኖች እየበረከቱ መጥተዋል፡፡ አንደ ሐዋርያው ስለ ወንጌል የታሰሩ ፣ በእሳት በስለትየተፈተኑ ቅዱሳንን ማሰብም እንደማይፈልጉ በግልጥ መናገርም ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ቀድመው ቢወለዱ ኖሮ ሰልፋቸው ከቅዱስ ጳውሎስጋር ከተጣሉት ሰዎች ጋር እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡
ቅዱስጳውሎስም ሆነ ሐዋርያቱ የታሰሩት ስለ ክርስቶስ ነበር፡፡ ጌታችን ‹እናንተን የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል› ብሎ ተናግሮላቸዋል፡፡ባለ ሽቱዋ ማርያም የሽቱ ዕቃ ሰብራ በጌታ እግር ሥር ስላፈሰሰች ‹ወንጌል በሚነገርበት ሥፍራ ሁሉ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆንይነገራል› ብሎ ጌታችን ገድሏ እንዲነገር አዝዞላት ነበር፡፡ (ማቴ.26፡13) ለበደለኛዋ ሴት መታሰቢያዋ ይነገር ብሎ ካዘዘላትበሃሳብዋ ሳይቀር ንጽሕት ስለሆነችው እመቤታችን ቢሰበክ ምኑ ላይ ነው ጥፋቱ? ጠርሙስ ሰብራ ሽቱ ላፈሰሰችው ሴት ታሪኳ ከተነገረ አንገታቸውን ሰብረው ደማቸውን ስላፈሰሱሰማዕታት ቢነገር ምን ይደንቃል? በዝሙት ስለኖረችው ሴት ከተሰበከ ስለ መነኮሳቱ ስለቅዱሳኑ ቢነገርየሚበዛ ይሆን ይሆን? ቅዱሳንን እየጠሉ ክርስቶስን እሰብካለሁ ማለት አይቻልም፡፡ ጌታምእኔን ከጠሩኝ ይበቃል አይልም፡፡ ለሳሙኤል ‹እኔን እንጂ አንተን አልናቁም› እንዳለው ቅዱሳኑን መናቅ እሱን መናቅ ነው፡፡ /1ሳሙ.8:7/
አንዳንዶች‹‹ስለ ቅዱሳንና ስለ ድንግል ማርያም ባለመስበካችን ነው ተቃውሞ የሚበዛብን ፤ እኛ ስለ ክርስቶስ ብቻ ነው የምንሰብከው›› ብለውራሳቸውን እንደ ሐዋርያት ፣ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ቤተ አይሁድ ሊያስመስሉ ይሞክራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እንኳን እንዲህ ዓይነትአቀራረብ የለውም፡፡ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ ‹እግዚአብሔር ኃያል ነው ፣ ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን ፣ እልል በሉ› በሚሉ ቃላትየተሞላ አይደለም፡፡ ስለነ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ ፣ ስለ ኖኅ ሙሴና ሳሙኤል ፣ ስለ ነቢያት ፣ ስለ ሐዋርያት የሚተርከው ክፍልይበዛል፡፡ ጌታችንም ነቢያቱን ቅዱሳኑን እያነሣ አስተምሯል፡፡ ይህ ማለት ስለ እሱ አልተሰበከም ማለት አይደለም፡፡ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻውበሰዎች ሕይወት ውስጥ የምናገኘው የእግዚአብሔርን ቸርነት ፣ ኃያልነትና ምሕረት ነው፡፡ ስሙ ሳይነሣ እንኳን የእሱን ስም ተሸክመውየተጋደሉ የቅዱሳን ሕይወት የእሱን አምላክነት ፍንትው አድርጎ ያሳየናል፡፡ ቅዱሳኑም ያለ እርሱ ምንም ማድረግ እንደማይቻላቸው አስተምረውናል፡፡
ለዘመናችን‹አጽራረ ቅዱሳን› መገለጫ አንድ የሰማሁትን ማሳያ ላስቀምጥ፡፡ በዕለተ ትንሣኤ አንዱ ‹ሰባኪ› ሊያውም በባዕድ ሀገር ላሉ ምዕመናን‹ድንጋዩን ማን ያንከባልልናል?› በሚል ርዕስ ያስተምራል፡፡ ሲያብራራው ‹‹ዛሬ ክርስቶስንእንዳናይ የከለከሉን ብዙ ድንጋዮች አሉ...›› ብሎ ጀመረ፡፡ ‹የከለከሉን ድንጋዮች› ብሎ የተረጎመው ግን ለቅዱሳን ነበር፡፡ የተናገረውክህደት መሆኑ የገባቸው ምእመናንም ፈጽሞ ሳያስታቸው አንገቱን አንቀው ከስፍራው አወረዱት፡፡ በጣም የሚገርመው ግን ‹ድንጋዩን ማንያንከባልልናል› በሚለው ዐረፍተ ነገር ቅዱሳንን ‹ድንጋይ› አድርጎ ሲተረጉም ያላገናዘበው ነገር አለ፡፡ ‹ድንጋዩን ማን ያንከባልልናል›ብለው የተናገሩት ራሳቸው ቅዱሳኑ ነበሩ፡፡ ቅዱሳን ደግሞ ‹እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ› ብለው መንገድ የሚያሳዩንናቸው እንጂ መንገድ የሚዘጉ አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር ያሳያችሁ እነዚህ ሰዎች ቅዱሳንን እንደዚህ ጠልተው እንዴት መንግሥቱን ይወርሳሉ? አብርሃምን እየጠሉ እንዴት ከአብርሃም እቅፍ ለመግባት ይታሰባል?(ሉቃ. 16) አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብን አናነሳም እያሉ እንዴት አድርገው ‹‹ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ››? ማቴ. 8፡11 ታቦት ዘዶርየተባለች እመቤታችን ወዳለችበትስ እንዴት መግባት ይቻላቸዋል?
‹‹ስለድንግል ማርያም አንሰብክም›› ባዮቹ ደግሞ የበለጠ ያስደንቃሉ፡፡ እኛ እመቤታችንን እንኳን ላለማመስገን ልናንገራግር ይቅርና በጸያፍአንደበታችን ስምዋን ስለጠራን እንሳቀቃለን፡፡ መጽሐፍ ‹ስለ ጽዮንዝም አልልም› ይላል፡፡ ጽዮን ከተማ ናት ካሉ እንኳን ለከተማ ዝም አልልም ከተባለ ዘጠኝ ወር ስለከተመባት ስለእግዚአብሔር ከተማእንዴት ዝም እንላለን? ‹ወንጌል ነው የምንሰብከው› የሚል ሰው ስለ እመቤታችን እንዴት አልናገርም ይላል? እመቤታችን የኖረችውበኦሪት ነው እንዴ? እስዋ ባትኖር ኖሮ ወንጌል አይጻፍም ነበር፡፡ ስለ እርስዋሳይናገሩ ምን ዓይነት ወንጌል መስበክ ይቻላል? የእርስዋን ስም ሳያነሱ የልደቱን ታሪክ እንዴት መተረክ ይቻላል?የእርስዋን ስም አውጥቶ ስደቱን መናገርስ እንዴት ይሆናል? በቃናው ሰርግ ቤት ያለ እርስዋ ስምና ሚና የተቀዳ ወይንስነበረ? በመስቀል ላይ በደም ተለውሶ እንኳን ስለ እናቱ ተናግሯል፡፡ እኛ ከቤተ መቅደስ የሰማነው ‹ግነዩለእግዚአብሔር ወጸውዑ ሰሞ ፤ እንዘ ኢትፈልጡ እሞ› /መልክአ ቁርባን/ ሲባል ነው (በግጥም ብንተረጉመው ‹ለእግዚአብሔር ተገዙ ፣ ስሙንም ጥሩ ፤ እናቱንም ሳታስቀሩ›እንደማለት ነው /ሳትለዩ/) ስለዚህ እመቤታችንን ሳልጠራ ክርስቶስን እሰብካለሁ የሚሉ ሰዎች ‹‹በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስያወራሉ።›› ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቶቹን ሰዎች ‹ስለ ክርስቶስ ይሰብካሉ› አይደለም ያለው ‹ያወራሉ› ነው፡፡ ግሡን ይዘንስናራባው ንግግራቸውም ስብከት ሳይሆን ‹‹ወሬ›› ነው ፤ እነርሱም ‹ወሬኞች› ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች
ስለ ክርስቶስየሚሰብኩት ለክርስቶስ ካላቸው ፍቅር ሳይሆን ለቅዱሳን ካላቸው ጥላቻነው፡፡ ይህም የሃሳባቸው ቅንነት ማጣት ውጤቱን ተራ ወሬ ያደርገዋል፡፡
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
12/06/2006 ዓ.ም.
No comments:
Post a Comment