Wednesday, 5 March 2014

“ሥጋውን ደሙን እንደተቀበለ ይሆንለታል፡፡” [መቅድመ ተኣምረ ማርያም]


“ሥጋውን ደሙን እንደተቀበለ ይሆንለታል፡፡” [መቅድመ ተኣምረ ማርያም]
      ተኣምረ ማርያም በእግዚአብሔር ፈቃድ በእመቤታችን ስም የተሰየመ የእግዚአብሔር ተኣምር ነው፡፡ ተኣምረ ማርያምን ከአረብኛ ወደ ግዕዝ እንዲተረጎም ያደረጉት ብእሴ እግዚአብሔር(የእግዚአብሔር ሰው) አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ናቸው፡፡ መጀመሪያ ወደ መቅድመ ተኣምረ ማርያም ትርጓሜ ከመሄዳችን በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ እንደሚያስፈልገው እናውሳ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ ያስፈልገዋል፡፡ 2ኛ.ቆሮ. 3፡6 “ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወት ይሰጣል፡፡” በማለት ጥሬ ንባብ ይገድላል፤ መንፈስ(ምሥጢር) ግን ያድናል በማለት ሐራሴ ወንጌል(የወንጌል ገበሬ) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይመሰክራል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥሬ ንባባቸው ላይ ምሥጢር የለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከበድ ያሉ ጽነት(የሚከብድ፣በደረቁ ሲታይ የተጣመመ) ያላቸው ቃላት አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ አምላክ፤ ፈጣሪ ሆኖ ሁሉን በፈቃዱ የሚያደርግ ንጉሥ ሆኖ ሳለ “መንፈስም ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፡፡” ማቴ.4፡1 በማለት ይናገራል፡፡ ይህን ቃል በቃል ወስደን መንፈስ ቅዱስ ወልድን ኢየሱስ ክርስቶስን ወሰደው ብንል ትልቅ ሕጸጽ ነው፡፡ ኑፋቄም ነው፡፡ ሌሎችም አሉ፤ ከእኔ አብ ይበልጣል፤ እግዚአብሔር አስነሳው….ወዘተ… የሚሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃላት በቀጥታ እንዳለ ብንተረጉመው እንስታለንና ስናነብ ከላይ አርዕስቱን ከሥር ኅዳጉን ማየት ግድ ይለናል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን በንባብ፣ በዜማና በትርጓሜ ትምህርት ቤቶችም እንደዚህ ዓይነት ቃላት ወይም ዜማዎች አሉ፡፡ በንባብ ትምህርት ቤት ለመያዝ የሚያስቸግሩ ቀለማት ጸዋጋት ቀለማት ይባላሉ፡፡ ክፉዎች ቀለሞች እንደማለት ነው፡፡ ይኼ ማለት ቀለማቱ ሕጸጽ ናቸው ለማለት ሳይሆን ዜማ ቤት ከሆነ አስመስሎ ዜማውን ለመጮኽ በጣም የሚከብድ ሲሆን፤ በንባብ ቤት ደግሞ ቀለማቱን ለመያዝ ወይም ለማንበብ የሚያስቸግሩ ከሆነ ጸዋጋት ቀለማት ይባላሉ፡፡ መጋቢያነ ምሥጢር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ዓይነት ለመረዳት አስቸጋሪ የሆኑ ገጸ ንባባትን በመጽሐፍ ቅዱስ ብናገኝ ማድረግ ስላለብን ነገር ሲመክሩ መቅድመ ወንጌል አንድምታ ላይ “ስታነብ ድንገት የሚከብዱ ቀለማትን ብታገኝ ዝም ብለህ አትለፋቸው፤ መልሰህ መላልሰህ ከላይ አርዕስታቸውን ከስር ኅዳጋቸውን በደንብ በማመሳከር አንብብ እንጂ ዝም ብለህ አትለፍ፡፡” በማለት መክረውናል፡፡
ለመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በአዋልድ መጻሕፍት ለመረዳት የሚጸኑ(የሚከብዱ) ቃላት/ሐረግ/ ስናገኝ፡-
፩. መጸለይ ይገባል፡፡ በቀደምት ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንተ ዘንድ ያልተረዱት፤ ያልተገለጸላቸው ምሥጢር ወይም የከበዳቸው ቃል ሲኖር ሱባኤ ገብተው በጾም በጸሎት ተወስነው ምሥጢሩን ይፈቱ ነበር፡፡ ምክንያቱም ንባብ ተሰጥቶት፤ መተርጎም የማይችል ይኖራል፡፡ ለምሳሌ የግዕዝ ቋንቋ ንባብ በደምብ እየቻለ ግን የማይተረጉም እንዳለ ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ይኼን ዓይነቱን “ስለዚህ በልሳን የሚናገር እንዲተረጉም ይጸልይ፡፡” 1ኛ.ቆሮ.14፡13 በማለት በልሳን መናገር አንድ ጸጋ ነው፡፡ በልሳን የተነገረውን መተረጎም ደግሞ ሌላ ጸጋ ነው፡፡ ስለዚህ በልሳን የተነገረውን ለመተርጎም መጸለይ ካስፈለገ ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተጻፉትን ቃላት ለመተርጎም መጸለይ እንዴት አያስፈልግ?
፪. መላልሰን ማንበብ፤ መትጋት፤ መጻሕፍትን ማገላበጥ ያስፈልጋል፡፡
፫. ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን መጠየቅ፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ “የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” ሐዋ.8፡31 በማለት ትርጓሜውን የማናቀው፤ ምሥጢሩ ሲርቀን ወደ አበው አባቶች ቀርቦና ጠልቆ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ንግባእኬ ሀበ ጥንተ ነገር(ወደ ቀደመው ነገር እንመለስ)! ቅዱሳት መጻሕፍት በሁለት ይከፈላሉ፡፡
፩.አስራው መጻሕፍት፤ 81ዱ መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ነው፡፡ አስራው ማለት ሥሮች፤መሠረቶች፤ አሳዳጊዎች ማለት ነው፡፡ለተቀደሰ መጽሐፍ ሁሉ ምንጮች፤ ሥሮች ናቸውና፡፡
፪. አዋልድ መጻሕፍት፤ ገድላት፤ ድርሳናት፣ ተኣምራት ንና ሌሎችንም ያጠቃልላል፡፡ አዋልድ ማለት በግዕዝ ሲሆን ልጆች ማለት ነው፡፡ ልጅነታቸውም ለመጽሐፍ ቅዱስ ነውና መጽሐፍ ቅዱስ የአዋልድ መጻሕፍት አባታቸው ነው፡፡ ስለሆነም አዋልድ መጻሕፍት በይዘት ና በባሕርይ መጽሐፍ ቅዱስን ይመስላሉ እንጂ በገጽ ብዛት ወይም በቅርጻቸው መጽሐፍ ቅዱስን ይመስላሉ ማለት አይደለም፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጎመላቸው፡፡” ሉቃ.24፡27 በማለት የቅዱሳት መጻሕፍት ምሥጢር የሚገለጸው ባለቤቱ እግዚአብሔር ሲገልጽ ብቻ መሆኑን አስተምሮናል፡፡ መናገርና መተርጎም ተለያይተው የሚሰጡ መንፈሳዊ ሀብቶች ናቸው ማለት ነው፡፡
 ተኣምረ ማርያም እመቤታችን ከእግዚአብሔር ተለይታ የሰራችው ተኣምር አይደለም፡፡ እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ እንዳለ ጌታ፤ዮሐ.15፡1፡፡ ቅርንጫፎቹም ቅዱሳን ናቸውና ፍሬውም የምናገኘው ቅርንጫፉ ከግንዱ ጋር እስካለ ድረስ ነውና ያለ እግዚአብሔር እርዳታ አንዳች ተኣምር አይደረግም፡፡ በዮሐ.15፡5 “እስመ ዘእንበሌየሰ አልቦ ዘትክሉ ገቢረ ወኢምንተኒ--- ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፡፡”እንዲል፡፡ ተኣምሩን ተኣምረ እግዚአብሔር ቢባልስ ለምን ተኣምረ ማርያም ይባላል ቢሉ ተኣምረ እግዚአብሔር ቢሉ አይደንቅም፤ እግዚአብሔር እራሱ ቢሰራው ምን ይደንቃል? የሚሳነው ነገር የለምና!! በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም አድሮ ይኼን ተኣምር መሥራቱ ግን ወይ የእግዚአብሔር ሥራ! በእናቱ የሰራውን ሥራ እዩ እንዲባል፤ ተኣምሩን በእመቤታችን አድሮ ገለጸ፡፡ ወንጌሉ የጌታ ሆኖስ ሳለ የማቴዎስ ወንጌል፤ የማርቆስ ወንጌል፤ የሉቃስ ወንጌልና የዮሐንስ ወንጌል ይል የለምን? ወንጌሉ የማቴዎስ ስለተባለ የጌታን ክብር ይሸፍነዋል? ወንጌል የሚናገረው ነገረ ክርስቶስ ቢሆንም ቅሉ ጸሐፊው ማቴዎስና ለመታሰቢያነቱ የማቴዎስ ወንጌል ተባለ፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ተኣምረ ማርያም የእግዚአብሔር ሥራ ሆኖ ሳለ መታሰቢያነቱ በእመቤታችን ስም ሆኖ ተኣምረ ማርያም ተባለ ማለት ነው፡፡
 “የታወቀ ምክንያት ካልከለከለው” ፤ ተወዳጆች ሆይ! ምንድነው የታወቀ ምክንያት? ለምሳሌ፡- ፩. ሐዘን፤ ሐዘን ተናግሮ አይመጣምና ድንገት በክርስቲያን ሰንበት ዕለተ እሑድ የታወቀ ምክንያት ሐዘን(ልቅሶ) ካልከለከለው ማለት ነው፡፡ ፪. ደዌ ፤ ሰው ሲታመም፤ ደዌ ሲያገኘው ነገ እታመማለሁ ብሎ አይደለምና የታወቀ ምክንያት ደዌ(በሽታ፤ሕመም) ካልከለከለው ማለት ነው፡፡ ፫. ኃጢኣት፤ መቼስ ሰው ሥጋ ወደሙን ለመቀበል በምክረ ካህኑ ቀኖና ከኃጢኣት በሽታ በንስሐ መፈወስ አለበትና የታወቀ ምክንያት እራሱን ለካህን ያላሳየ ኃጢኣተኛ የታወቀ ምክንያት ኃጢኣቱ ካልከለከለው ማለት ነው፡፡ ልብ በሉ! የታወቀ ምክንያት እኒዚህ ከላይ የጠቀስናቸውና ሌሎችም አሳማኝ ምክንያቶች ካልከለከሉት ተኣምሯን ሰምቶ ሥጋ ወደሙን ይቀበል ይላል መቅድመ ተኣምረ ማርያም፡፡ ሥጋ ወደሙን መቀበል ካልተቻለው ማለትም እነዚያ የታወቁ ምክንያቶች ከገጠሙት ግን ተኣምሯን ሰምቶ ይሂድ፤ ሥጋ ወደሙን እንደተቀበለ ይሆንልኛል፤ ይደረግልኛል ብሎ ይመን ማለት ነው፡፡ አስተውሉ! ሥጋ ወደሙን መቀበል ካልተቻለው አለ እንጂ ካልፈለገ አይልም!!! ቃሉ ልቅም ያለ የተነቀሰ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን በተለይ በዕለተ እሑድ መጥቶ የማያስቀድስ ከሆነ ተኣምረ ማርያም ላይ እንደተጻፈው አበው አውግዘዋል፡፡ ማውገዝ ማለት አንተ ከሃዲ፤ መናፍቅ ማለት ብቻ ሳይሆን አውግዘናል ማለት ቤተ ክርስቲያንን በእሑድ ዕለት የማይመጣ ገስጸናል፤ ነቅፈናል ማለት ነው፡፡ መንቀፍ ማውገዝ ተብሎ ሊነገር ይችላልና፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቶች ብዙ አገላለጦች አሉት፡፡ ለምሳሌ መፋታት ኃጢኣት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ባልና ሚስት አንድነት መክሮ፤ መፋታት ኃጢኣት መሆኑን አጥብቆ ካዘከረ በኋላ ድንገት ባልና ሚስት ሳይስማሙ “ቢለያዩ ግን ሚስት ሳታገባ ትኑር” ይላል፡፡1ኛ.ቆሮ.7፡10ና11፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ቢለያዩ ግን አለ እንጂ ቢፋቱ ግን አላለም፡፡ መፋታት ኃጢኣት ነውና፡፡ ስለሆነም ተኣምረ ማርያም ሥጋ ወደሙን አትቀበሉ አይልም!! ሥጋ ወደሙን ተቀበሉ ይላል እንጂ፡፡ ዳሩ ግን መቀበል ካልተቻለውስ? ይህ ሰው ይሙት? ተኣምረ ማርያም ግን ተስፋ ይሰጣል፤ በርታ አይዞህ ተኣምረ ማርያምን ስትሰማ ወደ ሥጋ ወደሙ በይበልጥ ትቀርባለህ አለ እንጂ ሥጋ ወደሙን የተቀበለና ተኣምረ ማርያምን የሰማ እኩል ናቸው አይልም፡፡ ቆራቢዎች ሁሉ ተኣምረ ማርያም እየሰሙ አይደል ሚቆርቡት? ተኣምረ ማርያም በመስማቴ መቁረብ ቀረልኝ የሚልስ አለ? ሥጋ ወደሙን እንዳንቀበል የሚከለክሉን ምክንያቶች ተኣምረ ማርያምን ከመስማት አይከለክሉንምና፡፡ ብዙዎች የተሐድሶ አርሲሳን(መናፍቃን) “እንደተቀበለ ይሆንለታል” የሚለውን ይዘው ተኣምረ ማርያምን  ከሥጋ ወደሙ ጋር እኩል የሚያደርግ አገላለጥ ይላሉ፡፡ እውን ነው? 1ኛ.ጴጥ.1፡24-“ሥጋ ሁሉ እንደሣር፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤” ይላል፡፡ ሥጋ ሁሉ እንደሣር ማለት ሥጋ ሣር ነው ማለት ነው? ተኣምረ ማርያም ሥጋ ወደሙን እንደተቀበለ አለ እንጂ ሥጋ ወደሙን ተቀብሏል አይልም፡፡ ጌታችንም ከትንሳኤ ሙታን በኋላ ስላለው ስለ ሰው ልጆች በመንግሥተ ሰማያት ስለሚኖረው አኗኗር ሲገልጽ “በትንሳኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡም፡፡” ማቴ.22፡30 ሲል  እንደ እግዚአብሔር መላእክት ማለት ሰዎች መላእክት ይሆናሉ ማለት ነው? እንደ ስለሚል ሰዎች ተቀይረው መላእክት ይሆናሉ ማለት አይደለም፡፡ ደግሞስ ንስሐ የበደለን እንዳልበደለ፤ ዘማዊውን እንደ ድንግል ታደርገዋለች ማለት በድሎ ንስሐ የገባና ምንም ያልበደለ አንድ ናቸው ማለት ነው? ዘማዊውን እንደ ድንግል ታደርገዋለች ማለት ድንግልናቸውን ያጡና ደናግላን አንድ ናቸው ማለት ነው? አይደለም፡፡ እንዳውም “እነሆ አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” ዘፍ.3፡22 ማለት አዳም ወልድ(ኢየሱስ ክርስቶስን) ሆነ ማለት ነው? እንደ የምትለዋን ሁሉ እኩል መሆን ነው ካልን ምን ዓይነት ክህደት ውስጥ እንደምንገባ አስተዋላችሁ?  ስለዚህ ተኣምረ ማርያምን በእምነት ቢሰማ ይለናል፡፡ ካላመነማ ሥጋ ወደሙስ ሥጋ ወደሙ ይሆንለታል እንዴ? ይሆንልኛል ይደረግልኛል በማለት ቢሰማ የሚለው እምነት መሠረት ያደረገ ቃል ነው፡፡ ተኣምረ ማርያም እኮ እንደስሙ የተኣምር መጽሐፍ ነው፡፡ ተኣምር ደግሞ ጠባዩ ልዩ ነው፤ በጥቅስ የሚገደብ አይደለም፡፡ አንድ ነገር በተጻፈለት ሕግ ሲሄድ ተኣምር አይባልም፡፡ ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ ሲሆን ተኣምር ይባላል፡፡ እንዳውም በምሳሌ፣ በሐተታ የማያምን ሰው ማመን ያለበት ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ብሎ ነው፡፡ ስለሆነም ተኣምረ ማርያምን የሚተቹ ሰዎች የማያምኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ተኣምረ ማርያምን ለመቀበል መሥፈርቱ እምነት ነውና፡፡ የተሐድሶ መናፍቃን በተኣምረ ማርያም መጽሐፍ ሳይሆን እራሳቸው የፈጠሩትን ሀሳብ ነው የሚነቅፉት፡፡ ስለሆነም ተኣምረ ማርያምን ሰምቶ ሥጋ ወደሙን መቀበል ይገባል፡፡ ነገር ግን ሥጋ ወደሙን እንዳንቀበል የታወቀ ምክንያት ቢገጥመን አልቆርብምና ብለህ ቤተ ክርስቲያን አትቅር፤ የቆረቡ ሰዎችና እኔ ያልቆረብኩት አንገናኝም ብለህ ተስፋ አትቁረጥ፤ ሳትጠራጠር ቤተ ክርስቲያን መጥተህ፤ ቃለ እግዚአብሔር፤ ተኣምረ ማርያም ብትሰማ፤ እነዚያ የቆረቡ ሰዎች ያገኙትን በረከት በእምነት አገኛለሁ ብለህ በፍጹም ልብህ እመን፤ ነገም በእምነትህ ለሥጋ ወደሙ ትበቃለህና ቤተ ክርስቲያን አትቅር ማለት ነው፡፡
የቀረውን ምሥጢር መንፈስ ቅዱስ ይግለጽልን፤ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፤ አሜን፡፡

1 comment:

  1. ሚስተር ቤንጃሚን የኢሜል ዝርዝሮችን እነሆ ፣ Lfdsloans@outlook.com ፡፡ / ወይም ደግሞ ንግዴን ለመጀመር በ 90,000.00 ዩሮ ብድር የረዳኝ WhatsApp + 1-989-394-3740 እና እኔ በጣም አመስጋኝ ነኝ ፣ እዚህ አንድ ነጠላ እናት ነገሮች እንዳላደረጉ መንገድ ለመፍጠር እየሞከርኩ ነው ፡፡ ከእኔ ጋር ቀላል ይሁኑ ግን ንግዴ እየጠነከረ ሲመጣ እና እያሰፋ ሲሄድ እያየሁ በሚስተር ሚስተር እርዳታ ፊቴ ላይ ፈገግታ አሳየኝ ፡፡ የገንዘብ ድጋፍን መፈለግ ወይም በዚያ ንግድ ውስጥ መከራን ማለፍ ወይም የመነሻ የንግድ ሥራ ፕሮጀክት መጀመር መፈለግ ይህንን ማየት እና ከችግራቸው ለመውጣት ተስፋ ሊኖረው ይችላል ... እናመሰግናለን ፡፡

    ReplyDelete