Tuesday, 27 January 2015


"ዝንየት" ና መንፈሳዊ ሥርዓቱ 
by ዘማርያም ዘለቀ

1). በየትኛውም መንገድ ቢሆን "ጸያፍ ሕልም" |ክፉ(መጥፎ) ሕልም|ን ያየ ወይም ዝንየት ያገኘው ሰው በዚያው ዕለት ሥጋ ወደሙ መቀበል (መቁረብ) አይችልም:: አንድ ሰው ሌሎች ለቁርባን የሚደረጉ ዝግጅቶችን ያሟላ ቢሆንም ሕልመ ሌሊትን በማየቱ ብቻ ቅዱስ ቁርባንን ለመቀበል ብቁ አይሆንም:: በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለ የሚከለከለው ከቅዱስ ቁርባን ብቻ አይደለም:: ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመግባትም ይከለከላል:: ለመግባት የሚፈቀድለት ልብሱን ካጠበ ወይም ከቀየረ ገላውን ከታጠበ በሗላ በማግስቱ ነው:: |ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን; ገጽ.24| ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት አይቻልም ሲባል ወደ ቤተ መቅደስ መግባት አይቻልም ማለት እንደ ሆነ ግልጽ ነው:: ስለዚህ ወደ ቤተ መቅደስ አይግባ እንጂ የመጀመሪያውን ቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ዘልቆ በመግባት ጸሎት; ትምህርትና የመሳሰሉትን መንፈሳዊ ተግባራት በዕለቱም ቢሆን ሊያከናውን ይችላል:: ቅዱስ ዳዊት "ጽዮንን ክበቧት እቀፏትም" በማለት እንደተናገረው በበዓል ቀናት ቤተ ክርስቲያንን ከቦ ማደር የተለመደ ነው:: በአንድ ወቅት ለበዓል ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመጡት ሰዎች መካከል ጥቂቶቹ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተኝተው ሳለ "ሕልመ ሌሊት" ታይቷቸዋል:: በዚህ ጊዜ መልአከ እግዚአብሔር ከእንቅልፋቸው ሳይነቁ ከቤተ ክርስቲያን አውጥቶ አርቆ ከውጭ አስተኝቷቸዋል:: ሰዎቹም በነቁ ጊዜ "ሕልመ ሌሊት" እንደመታቸው ከቤተ ክርስቲያንም የእግዚአብሔር መልአክ እንዳወጣቸው አስተዋሉ:: ይህ ታሪክ በእመቤታችን የተአምር መጽሐፍ ተጽፎ የሚገኝ ሲሆን "ሕልመ ሌሊት" ያገኘው ሰው ወደ ቤተ መቅደስ መግባት እንደሌለበት ተግባራዊ ትምህርት ያስተላልፋል:: በተጨማሪ በመኝታ ወቅት ሕልመ ሌሊትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ነገሮች ሊከሠቱ ስለሚችሉ በቤተ መቅደስ መኝታ ፈጽሞ የተከለከለ ነው:: መንፈሳዊ መጻሕፍትን የመረመረ ሰው ይህን የመሰለ ብዙ ታሪክ ያገኛል:: በቤተ ክርስቲያን የአፍንጫን ዛሕል(ንፍጥ) እንፍ ማለት ነውር እንደሆነ ሁሉ በሕልመ ሌሊት ተይዞ ሳለ ወደ ቤተ መቅደስ መግባትም እንዲሁ ነው:: በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ምራቃቸውን እየወረቁ ከዘበቱ አይሁዳዊያን ጋር እንዳትቆጠር በሕልመ ሌሊት ተነውረህ ሳለ ወደ ቤተ መቅደስ ተደፋፍረህ አትግባ:: ወደ ቤተ መቅደስ ገብተህ የምታገኘውን ፀጋ ሥርዓቷን ለማክበር ብለህ ከቤተ መቅደስ በአፍአ(በውጭ) ብትቆምም አታጣውምና::

 2).የፍትሕ መንፈሳዊ አንድምታ መጽሐፍ ስለ ጸሎት በተናገረበት አንቀጽ ከመኝታ ተነሥተው ስለሚፈጸሙ ጸሎተ ነግህ እና ጸሎተ መንፈቀ ሌሊት እንዲህ ብሏል:: "ይጸልዩ እምድኅረ ተሐጽቡ እደዊሆሙ በማይ ወለእመ ኢረከቡ ማየ በውእቱ ጊዜ ይንፍሑ እደዊሆሙ ወይሕጸቡ በምራቅ ዘይወጽእ እም አፋሆሙ::" ይህም "የነግሁንና (የንጋቱንና) የመንፈቀ ሌሊቱን ጸሎት እጃቸውን ከታጠቡ በሗላ ይጸልዩ; በዚያ ሰዓት ውኃ ባያገኙ እፍ ብለው በአፋቸው በሚወጣው ምራቅ እጃቸውን አሻሽተው ያማትቡ" ማለት ነው:: ይህ የፍትሕ መንፈሳዊ የጸሎት ሥርዓት ሐዋርያት በአብጥሊስ ያስተማሩትና የደነገጉት ሲሆን መጽሐፈ ሰዓታትም መግቢያ አድርጐታል:: መጽሐፈ ሰዓታት እንትፍ በማለት እጅን ማባበስ የሚሰጠውን ጥቅም ሲያትት "ወትከውን ንጹሐ እም ርዕስከ ወእስከ እገሪከ ዝ ውእቱ አምኃ መንፈስ ቅዱስ" ; "ይህ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነውና ከራስህ እስከ እግርህ ድረስ ንጹሕ ትሆናለህ" በማለት ይናገራል:: በሌላም ስፍራ "እስመ ማየ ዮርዳኖስ ይወጽእ እም አፉከ" እንደተባለው ሁሉ ካልተጠራጠሩ የዮርዳኖስ ውኃ ከአፍ ሊገኝ ይችላልና:: ፍትሐ ነገሥት መንፈሳዊ ከመኝታ ተነሥተው ስለሚፈጸሙ ሁለቱ የጸሎት ጊዜያት መተጣጠብ ያም ባይሳካ ምራቅን እንትፍ ብሎ መተሻሸት አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ሲያትት:- "ሰው ከተኛ ዝንየት አይጠፋምና" በማለት ይገልጻል:: ምናልባት ዝንየት ሊያገኘው ስለሚችል ተብሎ ሰው ሁሉ ከመኝታው በሗላ የሚያደርገውን ጸሎት ተጣጥቦ እንዲጸልይ ከታዘዘ ዝንየት እንዳገኘው እርግጠኛ የሆነ ሰው እንዴት የግድ መተጣጠብ ያስፈልገው ይሆን? አንዳንድ መምህራንና አባቶች በመኝታ ልብስ ጸሎት እንዳናደርግ የሚከላከሉትም በዚሁ ምክንያት ነው::

 3). ከዘር መንጠብ ጋር ተያይዞ የተሠራው ይህ ሦስተኛው ሥርዓት ባልና ሚስትን ብቻ የሚመለከት ነው:: ሩካቤ ያደረጉ ባልና ሚስት መተጣጠብን ምክንያት በማድረግ ከመጸለይ ወደሗላ ማለት የለባቸውም:: ሩካቤያቸው ንጹሕ ስለሆነ መላ አካላችንን ካልታጠብን አንጸልይም አይበሉ:: ለባልና ለሚስት ዘር የወጣበትንና የነጠበበትን አካል ማለትም ኀፍረተ አካልን ብቻ መታጠብ ይበቃቸዋል:: ይህ ሐሳብ በግዕዙ "ወኢይኅሥሡ ተሐፅቦ በቤተ ብለኔ ዘእንበለ ተሐፅቦ ዕድ ባሕቲቱ እስመ ሰብሳቦሙ ንጹሕ ውእቱ" ይላል:: "ተሐፅቦ ዕድ ባሕቲቱ" ማለት "እጅን መታጠብ ብቻ" ማለት ነው:: ባልና ሚስት "እጅን መታጠብ ብቻ" ይበቃቸዋል ማለት ወንድ አባለ ዘሩን ሴቲቱ ደግሞ አፈ ማኅፀንዋን መታጠባቸው ብቻ ይበቃቸዋል ማለት ነው:: ኀፍረተ አካል በመንፈሳዊ መጻሕፍት "እጅ" ይባላልና:: ለምሳሌ:- "ሕፅውኒ ኢገብረ አበሳ በዕዴሁ" የሚል ኃይለ ቃል ይገኛል:: ይህም "ጃንደረባም በእጁ በደል የለበትም" ማለት ሲሆን "እጅ" ተብሎ የተተረጐመው ኀፍረተ አካል ነው:: ጃንደረባ አባለ ዘርዕ የለውምና በሌላ ካልሆነ በቀር በአባለ ዘሩ በደል የለባትም እንደማለት ነው:: ስለዚህ ባልና ሚስት ምቹ ሁኔታ ካላቸው ከጸሎት በፊት መላ አካላቸውን መታጠባቸው የሚመረጥ ቢሆንም የሚጠበቅባቸው ግን ዘር የወጣበትንና የነጠበበትን ኀፍረተ አካል መታጠብ ብቻ ነው:: ይህ ሥርዓት ለሚስቶች ቀላል ይመስላል:: ምክንያቱም የግብር ውኃን መጠቀም በሴቶች ዘንድ የተለመደ በመሆኑ ነው:: ታዲያ ባሎች በሩካቤ ማግስት መላ ገላን መታጠብ ምቹ ባልሆነበት አጋጣሚና ቦታ ለጸሎት ከመቆማቸው በፊት ቢያንስ ንዑስ መሌሊታቸውን (ኀፍረተ አካላቸውን) መታጠብ እንዳለባቸው ያወቁ ኖሯል? ይህ አማራጭ ሥርዓት የተሠራው ሩካቤያቸው ንጹሕ በመሆኑ ለባልና ለሚስት ብቻ ነው እንጂ ሕልመ ሌሊት ላገኛቸው ላላገቡ ወጣቶች አይደለም:: ያላገቡ ወጣቶች ሕልመ ሌሊት ሲያገኛቸው መላ ሰውነታቸውን መታጠብ አለባቸው::