Tuesday, 27 January 2015


"ዝንየት" ና መንፈሳዊ ሥርዓቱ 
by ዘማርያም ዘለቀ

1). በየትኛውም መንገድ ቢሆን "ጸያፍ ሕልም" |ክፉ(መጥፎ) ሕልም|ን ያየ ወይም ዝንየት ያገኘው ሰው በዚያው ዕለት ሥጋ ወደሙ መቀበል (መቁረብ) አይችልም:: አንድ ሰው ሌሎች ለቁርባን የሚደረጉ ዝግጅቶችን ያሟላ ቢሆንም ሕልመ ሌሊትን በማየቱ ብቻ ቅዱስ ቁርባንን ለመቀበል ብቁ አይሆንም:: በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለ የሚከለከለው ከቅዱስ ቁርባን ብቻ አይደለም:: ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመግባትም ይከለከላል:: ለመግባት የሚፈቀድለት ልብሱን ካጠበ ወይም ከቀየረ ገላውን ከታጠበ በሗላ በማግስቱ ነው:: |ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን; ገጽ.24| ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት አይቻልም ሲባል ወደ ቤተ መቅደስ መግባት አይቻልም ማለት እንደ ሆነ ግልጽ ነው:: ስለዚህ ወደ ቤተ መቅደስ አይግባ እንጂ የመጀመሪያውን ቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ዘልቆ በመግባት ጸሎት; ትምህርትና የመሳሰሉትን መንፈሳዊ ተግባራት በዕለቱም ቢሆን ሊያከናውን ይችላል:: ቅዱስ ዳዊት "ጽዮንን ክበቧት እቀፏትም" በማለት እንደተናገረው በበዓል ቀናት ቤተ ክርስቲያንን ከቦ ማደር የተለመደ ነው:: በአንድ ወቅት ለበዓል ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመጡት ሰዎች መካከል ጥቂቶቹ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተኝተው ሳለ "ሕልመ ሌሊት" ታይቷቸዋል:: በዚህ ጊዜ መልአከ እግዚአብሔር ከእንቅልፋቸው ሳይነቁ ከቤተ ክርስቲያን አውጥቶ አርቆ ከውጭ አስተኝቷቸዋል:: ሰዎቹም በነቁ ጊዜ "ሕልመ ሌሊት" እንደመታቸው ከቤተ ክርስቲያንም የእግዚአብሔር መልአክ እንዳወጣቸው አስተዋሉ:: ይህ ታሪክ በእመቤታችን የተአምር መጽሐፍ ተጽፎ የሚገኝ ሲሆን "ሕልመ ሌሊት" ያገኘው ሰው ወደ ቤተ መቅደስ መግባት እንደሌለበት ተግባራዊ ትምህርት ያስተላልፋል:: በተጨማሪ በመኝታ ወቅት ሕልመ ሌሊትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ነገሮች ሊከሠቱ ስለሚችሉ በቤተ መቅደስ መኝታ ፈጽሞ የተከለከለ ነው:: መንፈሳዊ መጻሕፍትን የመረመረ ሰው ይህን የመሰለ ብዙ ታሪክ ያገኛል:: በቤተ ክርስቲያን የአፍንጫን ዛሕል(ንፍጥ) እንፍ ማለት ነውር እንደሆነ ሁሉ በሕልመ ሌሊት ተይዞ ሳለ ወደ ቤተ መቅደስ መግባትም እንዲሁ ነው:: በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ምራቃቸውን እየወረቁ ከዘበቱ አይሁዳዊያን ጋር እንዳትቆጠር በሕልመ ሌሊት ተነውረህ ሳለ ወደ ቤተ መቅደስ ተደፋፍረህ አትግባ:: ወደ ቤተ መቅደስ ገብተህ የምታገኘውን ፀጋ ሥርዓቷን ለማክበር ብለህ ከቤተ መቅደስ በአፍአ(በውጭ) ብትቆምም አታጣውምና::

 2).የፍትሕ መንፈሳዊ አንድምታ መጽሐፍ ስለ ጸሎት በተናገረበት አንቀጽ ከመኝታ ተነሥተው ስለሚፈጸሙ ጸሎተ ነግህ እና ጸሎተ መንፈቀ ሌሊት እንዲህ ብሏል:: "ይጸልዩ እምድኅረ ተሐጽቡ እደዊሆሙ በማይ ወለእመ ኢረከቡ ማየ በውእቱ ጊዜ ይንፍሑ እደዊሆሙ ወይሕጸቡ በምራቅ ዘይወጽእ እም አፋሆሙ::" ይህም "የነግሁንና (የንጋቱንና) የመንፈቀ ሌሊቱን ጸሎት እጃቸውን ከታጠቡ በሗላ ይጸልዩ; በዚያ ሰዓት ውኃ ባያገኙ እፍ ብለው በአፋቸው በሚወጣው ምራቅ እጃቸውን አሻሽተው ያማትቡ" ማለት ነው:: ይህ የፍትሕ መንፈሳዊ የጸሎት ሥርዓት ሐዋርያት በአብጥሊስ ያስተማሩትና የደነገጉት ሲሆን መጽሐፈ ሰዓታትም መግቢያ አድርጐታል:: መጽሐፈ ሰዓታት እንትፍ በማለት እጅን ማባበስ የሚሰጠውን ጥቅም ሲያትት "ወትከውን ንጹሐ እም ርዕስከ ወእስከ እገሪከ ዝ ውእቱ አምኃ መንፈስ ቅዱስ" ; "ይህ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነውና ከራስህ እስከ እግርህ ድረስ ንጹሕ ትሆናለህ" በማለት ይናገራል:: በሌላም ስፍራ "እስመ ማየ ዮርዳኖስ ይወጽእ እም አፉከ" እንደተባለው ሁሉ ካልተጠራጠሩ የዮርዳኖስ ውኃ ከአፍ ሊገኝ ይችላልና:: ፍትሐ ነገሥት መንፈሳዊ ከመኝታ ተነሥተው ስለሚፈጸሙ ሁለቱ የጸሎት ጊዜያት መተጣጠብ ያም ባይሳካ ምራቅን እንትፍ ብሎ መተሻሸት አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ሲያትት:- "ሰው ከተኛ ዝንየት አይጠፋምና" በማለት ይገልጻል:: ምናልባት ዝንየት ሊያገኘው ስለሚችል ተብሎ ሰው ሁሉ ከመኝታው በሗላ የሚያደርገውን ጸሎት ተጣጥቦ እንዲጸልይ ከታዘዘ ዝንየት እንዳገኘው እርግጠኛ የሆነ ሰው እንዴት የግድ መተጣጠብ ያስፈልገው ይሆን? አንዳንድ መምህራንና አባቶች በመኝታ ልብስ ጸሎት እንዳናደርግ የሚከላከሉትም በዚሁ ምክንያት ነው::

 3). ከዘር መንጠብ ጋር ተያይዞ የተሠራው ይህ ሦስተኛው ሥርዓት ባልና ሚስትን ብቻ የሚመለከት ነው:: ሩካቤ ያደረጉ ባልና ሚስት መተጣጠብን ምክንያት በማድረግ ከመጸለይ ወደሗላ ማለት የለባቸውም:: ሩካቤያቸው ንጹሕ ስለሆነ መላ አካላችንን ካልታጠብን አንጸልይም አይበሉ:: ለባልና ለሚስት ዘር የወጣበትንና የነጠበበትን አካል ማለትም ኀፍረተ አካልን ብቻ መታጠብ ይበቃቸዋል:: ይህ ሐሳብ በግዕዙ "ወኢይኅሥሡ ተሐፅቦ በቤተ ብለኔ ዘእንበለ ተሐፅቦ ዕድ ባሕቲቱ እስመ ሰብሳቦሙ ንጹሕ ውእቱ" ይላል:: "ተሐፅቦ ዕድ ባሕቲቱ" ማለት "እጅን መታጠብ ብቻ" ማለት ነው:: ባልና ሚስት "እጅን መታጠብ ብቻ" ይበቃቸዋል ማለት ወንድ አባለ ዘሩን ሴቲቱ ደግሞ አፈ ማኅፀንዋን መታጠባቸው ብቻ ይበቃቸዋል ማለት ነው:: ኀፍረተ አካል በመንፈሳዊ መጻሕፍት "እጅ" ይባላልና:: ለምሳሌ:- "ሕፅውኒ ኢገብረ አበሳ በዕዴሁ" የሚል ኃይለ ቃል ይገኛል:: ይህም "ጃንደረባም በእጁ በደል የለበትም" ማለት ሲሆን "እጅ" ተብሎ የተተረጐመው ኀፍረተ አካል ነው:: ጃንደረባ አባለ ዘርዕ የለውምና በሌላ ካልሆነ በቀር በአባለ ዘሩ በደል የለባትም እንደማለት ነው:: ስለዚህ ባልና ሚስት ምቹ ሁኔታ ካላቸው ከጸሎት በፊት መላ አካላቸውን መታጠባቸው የሚመረጥ ቢሆንም የሚጠበቅባቸው ግን ዘር የወጣበትንና የነጠበበትን ኀፍረተ አካል መታጠብ ብቻ ነው:: ይህ ሥርዓት ለሚስቶች ቀላል ይመስላል:: ምክንያቱም የግብር ውኃን መጠቀም በሴቶች ዘንድ የተለመደ በመሆኑ ነው:: ታዲያ ባሎች በሩካቤ ማግስት መላ ገላን መታጠብ ምቹ ባልሆነበት አጋጣሚና ቦታ ለጸሎት ከመቆማቸው በፊት ቢያንስ ንዑስ መሌሊታቸውን (ኀፍረተ አካላቸውን) መታጠብ እንዳለባቸው ያወቁ ኖሯል? ይህ አማራጭ ሥርዓት የተሠራው ሩካቤያቸው ንጹሕ በመሆኑ ለባልና ለሚስት ብቻ ነው እንጂ ሕልመ ሌሊት ላገኛቸው ላላገቡ ወጣቶች አይደለም:: ያላገቡ ወጣቶች ሕልመ ሌሊት ሲያገኛቸው መላ ሰውነታቸውን መታጠብ አለባቸው::

Monday, 9 June 2014

ለዘብተኛነት/ሊበራሊዝም/፡የክርስትና ዘመናዊው ጠላት - ክፍል 2

ሊበራል ክርስትና ምን አመጣ?

ሰዎች እግዚአብሔርን እንዳይፈሩ አደረገ
ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር የተባለው ተዘንግቶ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ የሚያሾፉ ፊልሞችን እንዲሠሩ፣ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣን እንኳን የማይለውን የዳቪንቺን ኮድን የመሰሉ አስተሳሰቦችን እንዲያራምዱ፣ በስቅለት ቅርጽ የፋሲካ ካንዲ እንዲሠሩ፣ ወዘተ አደረጋቸው፡፡ በየዘፈኖቻቸው ስመ እግዚአብሔርን እያነሡ እንዲቀልዱ አበረታታቸው፡፡ የጌታችን የስቅለት ሥዕል ከየቦታው እንዲነሣ አሠርቱ ትእዛዛት ከአሜሪካ ፍርድ ቤት በር እንዲነሣ አስደረጉ፡፡
ዛሬ ዛሬ ቅዱሳንን፣ ቤተ ክርስቲያንን እና የቤተ ክርስቲያን አካላትን እያነሡ መቀለድ እና ማቃለል በሀገራችን እየተለመደ ነው፡፡ ምሁራን፣ባለ ሥልጣናት፣ጋዜጠኞች እና ሌሎችም በይፋ በቤተ ክርስቲያን ነገሮች ላይ መቀለድ ልማድ አድርገውታል፡፡ የሚገርመው ነገር እነርሱም አይሰቀቁ፣እኛም ለምደነው እንስቃለን፤ አናዝንም፡፡ ለሌሎች አርአያ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ አገልጋዮች፣የእምነት አባቶች እና ገዳማውያን ሳይቀሩ በሥነ ምግባር ብልሹነት እና በሙስና እስከ መዘፈቅ ደርሰዋል፡፡
ለአክራሪ እስልምና አጋለጠን
አክራሪ እስልምና እጅግ በጣም ወግ አጥባቂ እምነት ነው፡፡ ይህ እምነት ወደ ምዕራቡ ዓለም ሲዘምት በሊበራሊዝም የተቦረቦረ ኅብረተሰብ ነው ያገኘው፡፡ ይህ የራሱ ማንነት የሌለው እና ሁሉም ትክክል ነው ብሎ የሚያምን ኅብረተሰብ ደግሞ በፍጥነት እና በፍላጎት ለሚሠራው አክራሪ እስልምና የተመቸ ሁኔታ ፈጠረለት፡፡ ፓትሪክ ሱኬዶ የተባሉ «የእስልምና እና ክርስትና ጥናት ተቋም ዳይሬክተር» እንደ ተናገሩት 200 ከፍተኛ የአሜሪካ ኩባንያዎች የሸሪያ ሕግን አጣጥመው ይሠሩበታል፡፡ ሳዑዲ ዐረቢያም ለዋና ዋና የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የገንዘብ ርዳታ በመስጠት የትምህርት ሥርዓቱ ከተቻለ ለእስልምና አመቺ ካልተቻለም ለዘብተኛ እንዲሆን ታደርጋለች ብለዋል፡፡
እጅግ ታዋቂ የሆኑ አሜሪካውያን ክርስትናው አላረካቸው ብሎ እስልምናን ሊቀበሉ የቻሉት፣ መጀመርያውኑ ርግጠኛውን ክርስትና ባለማግኘታቸው ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አንዳንድ የምዕራብ ዜጎች ከነ አልቃይዳ ጎን ተሰልፈው የገዛ ሀገራቸውን እና ወገናቸውን እስከማጥፋት የደረሱት ያሳደጋቸው ለዘብተኛ ክርስትና ሊያረካቸው ባለመቻሉ ነው፡፡
የሞራል መላሸቅን አስከተለ
ክፉ እና ደጉን ለይቶ የማያውቅ፣ ማንንም የማይፈራ፣ ለሱስ፣ ለመገዳደል፣ ለመጠጥ፣ ለሐሺሽ፣ ለዝሙት፣ ለጭፈራ፣ የተጋለጠ ለማኅበረሰባዊ እሴቶች ግድ የሌለው፣ ሀገሩን እና ወገኑን ለመርዳት የማያስብ፣ ከትምህርት ይልቅ መዝናናትን የሚመርጥ ትውልድ እንዲያፈሩ አደረገ፡፡ ዛሬ አሜሪካን ውስጥ ድራግ የማይቀምስ ወጣት የለም፡፡ በድንግልና መቆየት ነውር ሆኗል፡፡ ሌላው ቀርቶ አሜሪካውያን ለሂሳብ፣ ለፊዚክስ እና ለኢንጂነሪንግ ፍቅር የሌላቸው በሙዚቃ ግን የተለከፉ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ይሄ ነው፡፡ ቅዱሳንን ንቀው ታላላቅ ሰዎችን የሚያመልኩ፣ የፈለግኩትን ባደርግ ምን አለበት? በሚል ስሜት ለወንጀል የሚዳረጉ እንዲሆኑ አደረጋቸው፡፡
ቅድመ ጋብቻ የግብረ ሥጋ ግንኙነት እንደ ኃጢአት ሳይሆን እንደ መብት በመታየቱ ዛሬ ወጣቶቻቸው እምብዛም አይጨነቁበትም፡፡ በአሜሪካ ውስጥ በተደረገ ጥናት ዕድሜያቸው 20 ዓመት ከሞላቸው ወጣቶች መካከል ቢያንስ 75% ቅድመ ጋብቻ የጾታ ግንኙነት ፈጽመዋል፡፡ በነገራችን ላይ የዛሬ 2 ዓመት በአዲስ አበባ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በተደረገ ጥናትም 50% በላይ ተማሪዎች 18 ዓመት ሳይሞላቸው ጾታዊ ግንኙነት ማድረጋቸውን አመልክቷል፡፡
ጋብቻ በተጋቢዎች መካከል የሚኖር ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን መሆኑ እየቀረ በተፈለገ ጊዜ ሊቀር የሚችል መሆኑ ስለተሰበከ ፍቺ በርክቷል፡፡ ጋብቻ በአንደ ወቅት የሚፈጸም ሥነ ሥርዓት እንጂ የቅድስና ምንጭ መሆኑ እየተረሳ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሳይጋቡ በደባልነት መኖር እንደ ጋብቻ ኑሮ እየተቆጠረ መጥቷል፡፡
በአሜሪካ አብያተ ክርስቲያናቱ የጽንስ ማስወረድ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች ተብለው እስከ መለየት ደርሰዋል፡፡
አገልግሎትን እንደ ሞያ ማየት
በሊበራሊዝም አስተሳሰብ መንፈሳዊ አገልግሎቶች እንደ አንደ ሞያ ብቻ ይታያሉ፡፡ ጵጵስና፣ ካህንነት፣ ዘማሪነት፣ወዘተ ሞያዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም የሃይማኖት ሥነ ምግባርን እና አርአያ ክህነትን አይጠይቁም፡፡ አገልግሎት እንደሞያ ከታየ ፈሪሃ እግዚአ ብሔር ጠፍቶ ድፍረት ቦታውን ይይዛል፡፡ የሚያስተምሩትን ራሳቸው የማይፈጽሙ፣ለክብር ፣ለዝና እና ለገንዘብ ብቻ ሲሉ የሚያገለግሉ፣ በመንፈሳዊነት ስም ኃጢአትን የሚፈጽሙ አገልጋዮች እየበዙ ይሄዳሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት በአሜሪካ እና በአውስ ትራሊያ በካቶሊክ መነኮሳት ላይ የታየው የሞራል ዝቅጠት በሽታው የደረሰበትን ደረጃ ያመለክተናል፡፡
በሀገራችንም ቢሆን ዛሬ ዛሬ ምንኩስናን ለፍጹምነት መብቂያ መንገድ ሳይሆን የድብር አስተዳዳሪ ለመሆን፣ውጭ ሀገር ለመሄድ፣ የተሻለ ደመወዝ ለማግኘት የሚያስችል መንገድ አድርገው የሚቆጥሩት እየበዙ መጥተዋል፡፡ ሰባኪነት እና ዘማሪነትም ቢሆን ተሰጥኦ እና ትምህርት፣ሃይማኖት እና ምግባር የሚጠይቅ መሆኑ እየተዘነጋ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ቀላል እና ክፍት የሥራ ቦታም ይመስላል፡፡
የማይጾም፣ የማይጸልይ፣ የማያስቀድስ፣ ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የራቀ፣ የሌለበትን ሕይወት የሚያስተምር እና የሚዘምር አገልጋይ እየመጣ ነው፡፡ እንደ ባለሞያ ለእንጀራው ሲል ብቻ የማያምንበትን የሚያስተምር አገልጋይ እየመጣ ነው፡፡ ሰዓታት መቆም፣መቀደስ፣መመንኮስ፣ኪዳን ማድረስ፣ ጠዋት ተገብቶ ማታ የሚወጣበት ሥራ እየሆነ መጥቷል፡፡
ቤተ ክርስቲያን መዋቅር የማያውቃቸው ምእመናንን እና ካህናትን አፈራ
ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደው የማያስቀድሱ፣ የንስሐ አባታቸውን አግኝተው የማያውቁ፣ በአዳራሽ እንጂ በቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ ለመሰብሰብ የማይፈልጉ፤ አንድም ቤተ ክርስቲያን የማያውቃቸው ካህናት፣ ገዳም የማያውቃቸው መነኮሳት እየበዙ መጥተዋል፡፡
ከዚህም ብሶ ከአጠቃላዩ የቤተ ክርስቲያን መዋቅር የተነጠሉ አብያተ ክርስቲያናት እና ጳጳሳት ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ «እኔን ከመሰለኝ» የሚለውን የሊበራል አስተሳሰብ በመከተል በአንድ በኩል ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር እየተሰበሰቡ በሌላ በኩል ደግሞ የግላቸው ቤተ ክርስቲያን መሥርተው የሚንቀሳቀሱ ጳጳሳት ተፈጥረዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት የግል እና የመንግሥት ተብለው እንደ ሚከፈሉት ሁሉ አገልጋዮችም የግል አገልጋዮች እና የቤተ ክህነት አገልጋዮች ተብለን እስከ መከፈል ደርሰናል፡፡
የሊበራሊዝም ግርፍ የሆኑ አንዳንዶች ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ሊያድን እንጂ ሃይማኖት ሊመሠርት አልመጣም የሚል ፍስፍና ያስፋፋሉ፡፡ ለመሆኑ ሃይማኖት ምንድን ነው? ሃይማኖት ማለትኮ በቀላሉ ሲተረጎም እግዚአብሔርን የማምለኪያ መንገድ ማለት ነው፡፡ ታድያ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን መንገድ አልዘረጋም? ሐዋርያው ይሁዳስ «ለቅዱሳን አንድ ጊዜ የተሰጠች ሃይማኖት» በማለት የገለጠው ምንድን ነው?/ይሁዳ 1÷3/ ቅዱስ ጳውሎስስ በኤፌሶን መልእክቱ «አንድ ሃይማኖት አለ» ያለው/ኤፌ 4÷5¼ ተሳስቷልን? ልጁ ቲቶን «ስለዚህም ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም እኔ አንተን እንዳዘዝሁህ» ቲቶ 1÷5 በማለት የገለጠው ክርስትና የራሱ አደረጃጀት ስላለው አይደለምን?
ምን ይደረግ ?
ሊበራል ክርስትና ዛሬ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናትን እየተፈታተኑ ካሉት የዘመኑ ፈተናዎች አንዱ ነው፡፡ ይህ ፈተና በሁለት መልኩ ይገባል፡፡
የመጀመርያው አስተሳሰቡን በማራመድ ሆን ብሎ በሚደረግ ወረራ ነው፡፡ በሀገራችን ፕሮቴስታንቶች እና ተሐድሶዎች ሞክረውት የነበረው ይሄንን መንገድ ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን አንዳንድ ፖለቲከኞች፣ ፓስተሮች እና ተሐድሶዎች ይህንኑ አስተሳሰብ ያራምዱታል፡፡ የሁለት ዓመት መሠረትን በማጥፋት ቤተ ክርስቲያንን ያልተጣሩ አስተሳሰቦች መናኸርያ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ወንጌል የገባው ሕዝብ አልተፈጠረም፣ ክርስቲያኑ ክርስቶስን አያውቅም ነበር ብሎ ማሰብ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በቋንቋው ተርጉሞ እና ከዮዲት እና ግራኝ ጠብቆ ያቆየን ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን አታውቅም ነበር ብሎ በድፍረት ማስተማር መሠረትን ለማናጋት እንጂ እውነቱ ጠፍቶ አይደለም፡፡ አንድ ምሁር እንዳለው ይህ «ክርስቲያንን መልሶ ክርስቲያን ማድረግ  re  christianization of the Christians » ማለት ነው፡፡
በተለይም አሜሪካ የዚህ ወረራ ዋነኛ ቦታ ሆናለች፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት፣ትውፊት እና ባሕል እያቃለሉ ማስተማር፣ወይንም ደግሞ በጭራሽ ርእሰ ጉዳይ አድርጎ አለማስተማር እና ማስረሳት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ባለፉት ዘመናት 30 በላይ ገድላትን እና ድርሳናትን የሚሳደቡ ጽሑፎች በተሐድሶአውያን ታትመው በነጻ እየተሠራጩ ይገኛሉ፡፡  አክራሪ እስልምናን በተመለከተ ግን ትንፍሽ ብለው አያውቁም፡፡

ሁለተኛው ደግሞ አስተሳሰቡ ሳይታወቅ ይገባና ውስጥ ለውስጥ ይሸረሽራል፡፡ ከዚያም በሃይማኖት ለዘብተኛ ያደርጋል፡፡
ቅዱሳንን እና ክብራቸውን ማቃለል፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ስሕተት ለመፈለግ መኳተን፣ የጸሎት መጻሕፍትን አለመጠቀም፣ በሰበብ በአስባቡ ከጾም መሸሽ፣ በየምክንያቱ ከቤተ ክርስቲያን መራቅ፣ ለንዋያተ ቅድሳት ያለን አክብሮት መቀነስ፣ ምን አለበት በሚል ምክንያት ነገሮችን በፈለግነው መንገድ ማድረግ፣ ጳጳሳትን፣ ካህናትን እና አገልጋዮችን መናቅ፣ እና በድፍረት መናገር፤ ቤተ ክርስቲያን ባልሄድም በልቤ መልካም ሰው ከሆንኩ ይበቃኛል እያሉ መጽናናት፣ በሃይማኖት ጉዳዮች ሳቅ እና ቀልድ ማብዛት፣ በሃይማኖት ማፈር፣ አንዲት እምነት ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ወጥቶ፣ ለሌሎቹ ያዘኑ በመምሰል፣ ሁሉም ልክ ነው የሚል አዝማሚያ መያዝ ከበሽታው ምልክቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በሽታው ሌላም ምልክቶች አሉት፡፡ የሊበራል ክርስትና «እኔ እኔ» አስተሳሰብ ወደ መዝሙሩም፣ ወደ ትምህርቱም ይገባና ሁሉም በዚሁ ይቃኛል፡፡ እግዚአብሔርንም የኔ ማለት ይጀመራል፡፡ በትምህርታችን ውስጥ እኔ እንዲህ ሆኜ፣ ይህንን አድርጌ፣ እንዲህ ያለ ነገር ታይቶኝ፣ ወዘተ እያሉ ራስን ከፍ ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮችን መጨማመር፣ በመዝሙሮቻችንም ራስን መስበክ ይመጣል፡፡ በምሥራቃውያን ትውፊት ሰው ስለ ራሱ ይናገር የነበረው ታናሽነቱን፣ ትኅትናውን ወይንም በደለኛነቱን ለመግለጥ ነበር፡፡ ሊበራሊዝም ዘልቆ ሲገባ ግን የራስን ታላቅነት እና ክብር መናገርም ይጀመራል፡፡
ሊበራሎች ኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔር ነው ብለው አያምኑም፡፡ ከዚያ ይልቅ ለሰዎች ሕይወት «ሞዴል ነው» ይላሉ፡፡ ስለዚህም እንደ አንድ ፍቅረኛ፣ ጓደኛ፣ አርአያ ያዩታል እንጂ በአምላክነቱ አይቀበሉትም፡፡ በመሆኑም ናፈቀኝ፣ እወደዋለሁ፣ ጓዴ ነው፣ አብሮ አደጌ ወዘተ ብሎ መጥራት ያዘወትራሉ፡፡ ይህ አስተሳሰባቸው ገብቶብን እንደሆነም አላውቅም «ስትናፍቀን እንዘምራለን» የሚል መዝሙር በሰንበት /ቤቶች ሲዘመር የሰማሁ ይመስለኛል፡፡
ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን ከሁለት አቅጣጫ በሚመጣ ፈተና ተወጥራለች፡፡ ከምሥራቅ ወግ አጥባቂው እና በከፍተኛ ሁኔታ ኃይልን፣ ገንዘብን እና ነውጥን በሚጠቀመው አክራሪ እስልምና፣ ከምዕራብ በኩል ደግሞ ለሃይማኖት ግድየለሽ፣ በፈጣሪ በሚቀልደው እና ጠንካራ እና ጽኑዕ እምነትን ለመሸርሸር በተነሳው ሊበራል ክርስትና፡፡ አንዱ በኃይል ሌላው በፍልስፍና - ኦርቶዶክሳዊነትን ለማጥፋት ዘምተዋል፡፡
ይህንን ከሁለት ወገን የመጣ እና ሳንዱዊች ሊያደርገን የተዘጋጀ ፈተና «መንፈሳውያን ሃይማኖታውያን» በመሆን ብቻ ነው ድል የምንነሣው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በመዋቅር የተበታተነች፤ በአሠራርዋ የተዳከመች ከሆነች፤ ልጆቿ በመንፈስ የዛሉ፣ በሃይማኖት ዕውቀት ያልበረቱ ከሆኑ ፈተናውን መቋቋም አይችሉም፡፡
«በክርስትና እና በሳይንስ መካከል ያለው ዐቢይ ልዩነት፣ በሳይንስ የቅርቡ በጣም የተሻለ ሲሆን፣በክርስትና ግን የጥንቱ በጣም የተሻለ መሆኑ ነው in science the latest is the best, but in Christianity the oldest is the best» በማለት ይስሐቅ አል ባራኪ የተባሉ ሶርያዊ ሊቅ እና ሳይንቲስት ተናግረዋል፡፡ ክርስቲያን የሆንነው እኛ አባቶቻችንን ለመምሰል እንጂ አባቶቻችን እኛን እንዲመስሉን አይደለም፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያንም የመጣነው እኛ በቤተ ክርስቲያንዊ ትምህርት እና ሕግ ልንመራ እንጂ ቤተ ክርስቲያን በኛ ትምህርት እና ሕግ ለመምራት አይደለም፡፡
በመሆኑም ትክክለኛውን ክርስትና ለመኖር እኛም ወደ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተ ክርስቲያንም ወደ እኛ መግባት አለባት፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና በሦስት መልኩ መገለጥ አለበት ትምህርታዊ፣ ሊተርጂያዊ፣ እና ትውፊታዊ፡፡ ትምህርታዊ ማለት መጽሐፍ ቅዱስን አባቶቻችን በተረዱበት መንገድ እና መሠረት መረዳት፣ መመስከር እና መኖር ማለት ነው፡፡  በክርስትና አዳዲስ ማብራርያዎች እንጂ አዳዲስ መሠረተ ሃሳቦች ሊኖሩ አይችሉም፡፡
ሊተርጂያዊ ማለት ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት የሚገኙትን ጾም ፣ጸሎት፣ ቅዳሴ፣ የምሥጢራት ተሳትፎ፣ ዝማሬ፣ ወዘተ ገንዘብ ማድረግ እና የእነዚህ ፍሬዎች የሆኑትን የምግባር ፍሬዎች ማሳየት ማለት ነው፡፡ ትውፊታዊ ማለትም በቤተ ክርስቲያን ያገኘናቸውን የቀደሙ አበው የሕይወት መንገዶች፣ትሩፋቶች፣ጸጋዎች፣ ቅርሶች በመያዝ፣በመጠበቅ እና በመጠቀም መኖር ነው፡፡
ዋናን ከውኃ ውጭ መዋኘት እንደማይቻለው ሁሉ ክርስትናንም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ መኖር አይቻልም፡፡ በመርከቧ ሲጓዙ ማዕበል በተነሣባቸው ጊዜ በዚያው መርከብ ውስጥ ሆነው አድነን ነበር ያሉት ሐዋርያት፡፡ እኛም በየምክንያቱ ከቤተ ክርስቲያን መውጣታችንን ትተን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመኖር ችግሮችን መጋደል እና መቋቋም ያስፈልጋል፡፡

በረከታቸው ይደርብንና ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ «ሸረሪት አትሁኑ» ይሉ ነበር፡፡ ሸረሪት ድር አድርታ የኖረችበት ቤት ሲቃጠል ውኃ አምጥታ ከማጥፋት ይልቅ ቤቱን ለቅቃ ሌላ ቦታ በመሄድ ድር ታደራለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ፈተና በገጠማት ቁጥር እየሸሹ የራስን ኅሊናዊም ቁሳዊም ጎጆ መቀለስ ሸረሪትነት ነው፡፡
ሃይማኖት የትርፍ ጊዜ ሥራ መሆን የለበትም፡፡ መንፈሳዊነትም ባሕል እና ልማድ ብቻ ሆኖ ያለ ልቡና እንዲሁ የሚኖርበት መሆን የለበትም፡፡ በመሆኑም ቀጥ ብሎ ራስን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ እንደዋዛ የምንናገራቸው እና የምናደርጋቸው ነገሮች ቤተ ክርስቲያንን ሸርሽረው ሸርሽረው በምእመናን ላይ የማይጠገን ቁስል ከመጣላቸው በፊት በቀደሙት አበው ትምህርት እና ኑሮ መነጽርነት መንገድን እና ልብንም መመርመሩ የተሻለ ነው፡፡ 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ከቡር     By dn Daniel kibret (www.danielkibret.com)